በውጭ ሃገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና በመንግስት መካከል ሊካሄድ የታቀደ ስብሰባ መሰረዙ ተገለጸ

ኢሳት (ህዳር 7 ፥ 2009)

በውጭ ሃገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና በመንግስት መካከል ባሉ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ረቡዕ በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄድ የነበረ ስብሰባ ባልታወቀ ምክንያት መሰረዙ ተገለጸ።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቋቋመው የዳያስፖራ ማህበር ጽ/ቤት ከ1ሺ በላይ ሰዎች ይታደሙበታል ተብሎ የተጠበቀው የውይይት መድረክ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ሊካሄድ አለመቻሉንና ስብሰባው ለሌላ ጊዜ ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ተቋማት አስታውቋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደመቀ ኣጥናፍ ስብሰባው እንደማይካሄድ ከማህበሩ እንደተነገራቸውና ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንደማያውቁ ምላሽን ሰጥተዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት የዲያስፖራ ስብሰባውን ለማካሄድ ቅድመ-ዝግጅት ሊያደርጉ የቆየ ሲሆን፣ በዚሁ ስብሰባ ከውጭ ሃገር ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘ ተሳታፊ ይኑር አይኑር የታወቀ ነገር የለም።

ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ሃገራዊ ጉዳዮች ሊካሄድ ታስቦ በነበረው ውይይት ላይ ዋነኛ አጀንዳ ይሆናሉ ተብሎ ተጠብቆ እንደነበርም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።