አልሸባብ ከኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው የቲጌሎ ከተማ ማክሰኞ ተቆጣጠረ

ኢሳት (ህዳር 7 ፥ 2009)

የሶማሊያው ታጣቂ ሃይል አልሸባብ ከኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው የቲጌሎ ከተማ ማክሰኞ መቆጣጠሩ ተገለጸ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያዎችን መልሶ መያዝ የጀመረው ታጣቂ ሃይሉ በባኩል ግዛት የምትገኘውን የቲጌሎ ከተማ ለመቆጣጠር ለሰዓታት የቆየ የተኩስ ልውውጥና የአጥፍቶ መጥፋት ድርጊት መፈጸሙን መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘግበዋል።

ከኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ ትገኛለች የተባለችው የቲጌሎ ከተማ በቅርቡ በሶማሊያ የመንግስት ወታደሮች በቁጥጥር ስር ውላ እንደነበር ሬድዮ ሸበሌ በሪፖርቱ አቅርቧል።

ታጣቂ ሃይሉ ከተማዋን መልሶ ለመያዝ በወሰደው እርምጃ በትንሹ አራት የሶማሊያ መንግስት ወታደሮች መገደላቸው ቢገለጽም፣ የሃገሪቱ መንግስት ግድያውን አስተባብሏል። የኢትዮጵያ ወታደሮች ከያዟቸው ስፍራዎች መልቀቃቸውን ተከትሎ አልሸባብ በትንሹ አምስት ቁልፍ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያዎችን እንደተቆጣጠረም ታውቋል።

ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ በሃገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ቁልፍ ከተባሉ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው እንደወጡ በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ቆይተዋል።

የተለያዩ አካላት ኢትዮጵያ ወታደሮችን ለማስወጣት የጀመረችው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተገናኘ ነው ቢሉም የመንግስት ባለስልጣናት ጉዳዩን አስተባብለዋል።

የኢትዮጵያ ወታደሮች ከተለያዩ የማዕከላዊ ሶማሊያ መውጣታቸውን ተከትሎ አልሸባብ ታጣቂ ሃይል ይዞታዎችን እያጠናከረ እንደሚገኝ አልጀዚራ የቴለቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

ለሶማሊያ የጸጥታ ስጋት ሆኖ የቀጠለው ይኸው ቡድን ከኢትዮጵያና በሃገሪቱ ሰፍረው ከሚገኙ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ከአጠቃላይ አስር ከተሞችን እንደተቆጣጠረ ለመረዳት ተችሏል።