ኢሳት (ህዳር 7 ፥ 2009)
በአሜሪካ አገር በፊላዴልፊያና በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባሳለፍነው ቅዳሜ (November 12) ኢሳትን ለመደገፍ ያካሄዱት የገቢ ማሰባሰቢያ በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን አስተባባሪዎች ገለጹ።
በዚሁ የገቢ ማሰባሰቢያ ስርዓት ላይ የኢሳት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አበበ ገላው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እንዲሁም ኮሜዲያን ክበበው ገዳ የተገኙ ሲሆን፣ በወቅቱም ለጨረታ የቀረበው የአቶ በቀለ ገርባ እና የኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ ምስል ከ15 ሺ ዶላር በላይ መጫረቱን ለማወቅ ተችሏል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን በታደሙበት በዚሁ በዓል ላይ የፌላዴልፊያ የሴቶች ማህበር ለጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ያዘጋጁትን ሽልማት ያበረከቱ ሲሆን የፊላዴልፊያ የኢሳት ድጋፍ ኮሚቴ በተመሳሳይ ለጋዜጠኛ አበበ ገላው ሽልማት አበርክቷል።
የክብር እንግዶቹ ባደረጉት ንግግር፣ ለኢሳት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነትና ለፍትህ የሚያደርገውን መራራ ትግል እንደማጠናከር ይቆጠራል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ የኢሳትን 6ኛ አመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ ሰሞኑን በኖርዌይ መዲና ኦስሎ፣ እንዲሁም በስዊዘርላንድ ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መካሄዱን አስተባባሪዎች ለኢሳት አስታውቀዋል። በቀጣይም በዚሁ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችና ሌሎች አገራት ተመሳሳይ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት እንደሚካሄድ የኢሳት አለም አቀፍ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ገልጿል።