ኢሳት (ህዳር 6 ፥ 2009)
በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት በሃገሪቱ ተከስቶ ያለውን ፖለቲካዊ ውጥረት ዕልባት ለመስጠት የፖለቲካ ስርዓት ማሻሻያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርግ የሚያሳስቡ ሃገራት እየጨመሩ መምጣታቸውን አለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ስጋቷን ስትገልፅ የቆየችን ኖርዌይ፣ የካናዳ መንግስት ያቀረበውን አይነት የፖለቲካ ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረቧን አፍሪካ ኒውስ አስነብቧል።
የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦርጄ ብሬንድ (Borge Brende) በኢትዮጵያ አፈጣኝ የፖለቲካ ስርዓት ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲደረግ ማሳሰባቸውን የዜና አውታሩ አመልክቷል።
የካናዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሃገሪቱ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ሰኞ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በሃገሪቱ ተከስቶ ያለውን የፖለቲካ ውጥረትና አለመረጋጋት እልባት ለመስጠት የፖለቲካ ስርዓት ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ እንዲሁም በቅርቡ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች አጋር ሃገራት ተመሳሳይ ጥሪን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ይሁንና በቅርቡ ተግብራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የካናዳና የኖርዌይ መንግስታት ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ከማድረጉ በተጨማሪ ሁሉን አቀፍ የሆነ ሰላማዊ ውይይት እንዲያካሄድ በማሳሰብ ላይ ናቸው።
በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ስጋታቸውን እየገለጹ ያሉት እነዚሁ ሃገራት በተለይ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ያባብሳል ሲሉ ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
የኖርዌ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦርጂ ብሬንድ ሃገራቸው በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርብ እየተከታተለች እንደሆነም ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ባለፈው ወር ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ከ11 ሺ የሚበልጡ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን መንግስት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ይሁንና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ለእስር ተዳርገው የሚገኙት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን እየገለጹ የሚገኝ ሲሆን መንግስት እስካሁን ድረስ ታሳሪዎቹ እንዳይጎበኙ እገዳን ጥሏል።