ኢሳት (ህዳር 6 ፥ 2009)
ከየመን በግዳጅ እንዲወጡ ተደርገው በጎረቤት ጅቡቲ ከሰፈሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል በትንሹ 24ቱ መሞታቸው ተገለጸ።
መቀመጫውን በስዊሰርላንድ መዲና ጄኔቫ ያደረገው የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (IOM) የመን ስደተኞቹን በሃይል ወደፈለጉበት ቦታ እያጓጓዘች ያለችው ድርጊት እጅጉን አሳስቦት እንደሚገኝ ማክሰኞ አስታዉቋል።
ባለፈው ሳምንት 82 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በጀልባ ተጭነው በጅቡቲ ያለማንም ታዛቢነት ያለ በቂ ምግብና መጠለያ እንዲሰፍሩ መደረጋቸውን የስደተኛ ድርጅቱ ቃለ አቀባይ የሆኑት ኢታይ ቪሪሪ (Itayi Viriri) ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የጅቡቲ ባለስልጣናት ከነዚሁ ስደተኞች መካከል በትንሹ 24 የሚሆኑት ህይወታቸው እንዳለፈ ማረጋገጣቸውን ቃል-አቀባዩ አክለው ገልጸዋል።
የየመን ባለስልጣናት ኢትዮጵውያን ስደተኞቹን ከተለያዩ እስር ቤቶች በማውጣት ያለ በቂ ምግብና መጠለያ ወደ የመን በማጓጓዝ እየጣሏቸው እንደሚገኙ የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት አመልክቷል።
በተለያዩ ጊዜያት ወደ የመን የተሰደዱ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሃገሪቱ የሚገኙ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ስደተኞቹ በሃይል እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።
ከየመን በሃይል እንዲወጡ እየተድረጉ ያሉት ኢትዮጵያውያን ከምግብ ማነስ ከፍተኛ የአካል መጎሳቆል እንደሚታይባቸው የስደተኛ ድርጅቱ ቃል አቀባይ ቪሪሪ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2015 ዓም ከ70ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ጦርነት ዕልባት ወዳላገኘባት የመን መሰደዳቸውን የስደተኛ ድርጅቱ መረጃ የመለክታል።
በጅቡቲ በአሳዛኝ ሁኔታ ሞተዋል የተባሉትን ኢትዮጵያውያን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው ምላሽ የለም።