ኅዳር ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአማራ ክልል ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ባሉት የትምህርት እርከኖች ባለፉት አመታት ከታሰበው ግብ ለመድረስ እንዳልቻለ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ፡፡
አቶ ብናልፍ ሰሞኑን ከትምህርት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ስለዓለፈው ዓመት የትምህርት አፈጻጸም በተወያዩበት ጊዜ እንደተናገሩት አጠቃላይ የርብርብ ማዕከል ይሆናል ተብሎ በተያዘው ዕቅድ መሰረት በቅድመ መደበኛ፣በመጀመሪያ ደረጃ፣በሁለተኛ ደረጃ እና በመሰናዶ ትምህርት በዓመቱ ይሳካል ተብሎ የታሰበውን ያህል ሽፋኑ ላይ መድረስ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡
ክልሉ በልዩ ፍላጎት ማስተማር የቻለው ሰባ አምስት በመቶ ብቻ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ በሁለተኛ ደረጃ ልዩ ፍላጎት ትምህርት መስክ ከተያዘው ዕቅድ ሰላሳ ሰባት በመቶ ብቻ በማከናወን በዝቅተኛ አፈጻጸም ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
በጎልማሶች ትምህርት በደረጃ አንድና ሁለት ለማስተማር ታቅዶ ከነበረው ውስጥ መሸፈን የተቻለው ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ጎልማሶች መካከል ፣ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብቻ በመሸፈን በዝቅተኛ አፈጻጸም ዓመቱን በመጨረስ ከሽፋን አንጻር ችገሮች እንደታዩባቸው ተናግረዋል፡፡
ሃላፊው አክለውም ወደ ትምህርት ቤት መምጣት የነበረባቸው ህጻናት በየቤታቸው እንደሚገኙ ተናግረው ፣ የነዚህ ህጻናት ቁጥር ቀላል የሚባል እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ክልሉ ለትምህርት ከደረሱት ህጻናት መካከል ከዘጠኝ በመቶ በላይ የትምህርት እድል እንዳላገኙ ተናግረው በአጠቃላይ በሁሉም ፕሮግራሞች የታዩ አፈጻጸሞች መድረስ በሚገባው ደረጃ ላይ የደረሱ እንዳልሆኑ አረጋግጠዋል፡፡
ባለፈው ዓመት የአስረኛ ክፍል ሃገር አቀፍ ፈተና በአማራ ክልል ከፍተኛ የውጤት ማሽቆልቆል የታየበት መሆኑን የቢሮ ኃላፊው በዚሁ ውይይት ጊዜ ለባለሙያዎች የተናገሩ ሲሆን፣ በዚህ ብሄራዊ ፈተና ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲወዳደር ባለፈው ዓመት ከነበረው የአንደኛነት ደረጃ በመውረድ ሰባተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡ባለፈው ዓመት ሁሉንም ትምህርት ዓይነት ሙሉ በሙሉ ኤ ያመጡ ተማሪዎች ብዛት 1569 ሲሆን በዚህ ዓመት ግን 533 ብቻ መሆኑ ዓመቱ ከፍተኛ የውጤት ማሽቆልቆል የታየበት የወረደ አፈጻጸም የተገኘበት መሆኑን አልሸሸጉም፡፡