በኢትዮጵያ ማዕድን ፈልጋ ላይ ተሰማርቶ የነበረ ኩባንያ ፕሮጄክቱን መንግስት እንዲረከብለት ጠየቀ

ኢሳት (ህዳር 5 ፥ 2009)

በቅርቡ በኢትዮጵያ የአፋር ክልል የጀመረውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር የማዕድን ፍለጋ ስራ ለማቋረጥ የወሰነ አንድ የእስራዔል ኩባንያ መንግስት ፕሮጄክቱን እንዲረከብለት ጠየቀ።

I.C.L. የተሰኘ ይኸው አለም አቀፍ ኩባንያ የማዕድን ፍለጋ ስራውን ከተረከበው ሌላ ኩባንያ ጋር የተገናኘ 55 ሚሊዮን ዶላር የግብር ክፍያ ያለአግባብ ተጠይቄያለሁ በማለት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ቅሬታን መቅረቡ ይታወሳል።

የእስራዔሉ ኩባንያ የኢንቨስትመንት ስራውን ለማቋረጥ የወሰደውን ውሳኔ ተከትሎ በዚህ በአሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ ለሚገኙ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከድርጅቱ የባንክ አካውንት የገንዘብ ዝውውር እንዳይደረግ ትዕዛዝ አስተላልፎ እንደነበር መዘገባችን የሚታወቅ ነው።

ይኸው ኩባንያ በቅርቡ ለመንግስት በጻፈው ደብዳቤ ፕሮጄክቱን ሙሉ ለሙሉ እንዲረከበውና የፕሮጄክቱ መዝጊያ ማረጋገጫ ሰርቲፍኬት እንዲሰጠው ጥያቄ ማቅረቡን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በአንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት በአፋር ክልል የፖታሽ ማዕድን ፍለጋን ለማካሄድ እንቅስቃሴን ጀምሮ የነበረው የእስራዔል ኩባንያ ፕሮጄክቱን ለማቋረጥ መወሰኑን ተከትሎ በኢትዮጵያ የነበረው የባንክ ሂሳብ እና ንብረቶች ታግዶበት እንደነበር ይፋ አድርጓል።

ከመንግስት ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብቶ የሚገኘው ይኸው ኩባንያ በማዕድን ፍለጋ ዘርፍ ከፍተኛ ገንዘብን ሲመደብ የመጀመሪያው መሆኑም ታውቋል።

ኩባንያው ከኢትዮጵያ ጠቅልሎ ለመውጣት መወሰኑን ተከትሎ ወደ 10 የሚደርሱ የውጭ ሃገር የድርጅቱ ባለሙያዎች ከሃገር የወጡ ሲሆን፣ ወደ 145 ኢትዮጵያዊ ቋሚ ተቀጣሪዎችን ከተያዘው ወር ጀምሮ ማሰናበቱም ለመረዳት ተችሏል።

የእስራዔሉ ኩባንያ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ለሃገሪቱ በአመት የ300 ሚሊዮን ዶላር ውጭ ምንዛሪን እንዲሁም ለ3ሺ ሰራተኞች የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ እንድነበር ታውቋል።

ባለፈው አመት አንድ የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ ኩባንያ መንግስት የገባውን ቃል ተግባራዊ አላደረገም በማለት ከኢትዮጵያ ጠቅልሎ መውጣቱ ይፋ ማድረጉ  የሚታወስ ነው።