ኢሳት (ህዳር 5 ፥ 2009)
የግብፅ የውሃ ምህንድስና ባለሙያዎች በመገንባት ላይ ያለው የአባይ ግድብ ወደ ግብፅ የሚፈስ ውሃን በአመት በ12 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ይቀንሳል ሲሉ ስጋታቸውን ገለጹ።
ሁለቱ ሃገራት ግድቡ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለማስጠናት ከሁለት አለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ላይ ቢደርሱም የግብፅ ባለስልጣናት ጥናቱ ሳይጀመር ግድቡ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
በካይሮ ዩኒቨርስቲ የውሃ ሃብት ፕሮፌሰር የሆኑት ናድር ኑረዲን በመገንባት ላይ ያለው የአባይ ግድብ የግብፅን የውሃ ፍሰት በከፍተኛ መጠን በመቀነስ የናስር ሃይቅን ሊያደርቅ እንደሚችል መግለጻቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ጋዜጣ ዘግቧል።
ግድቡ ሃገሪቱ የምታገኘውን የውሃ ፍሰት በአመት በ12 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ይቀንሳል ሲሉም የውሃ ሃብት ምህንድስና ባለሙያው አስታውቋል።
በግብጽ የሚገኙ በርካታ የግብርና ፕሮጄክቶች በውሃ ፍሰቱ መቀነስ ምክንያት ድርቅ ሊያጋጥማቸውና ስራቸውንም ሊያቆሙ እንደሚችሉ የሃገሪቱ የውሃ ባለሙያዎች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ግድቡ በአካባቢው በየ10 አመቱ በሚከሰት የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በመሆኑም ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችልና ድርጊቱ በግብፅና በሱዳን መጠነ ሰፊ ጥፋትን ሊያስከትል እንደሚችል ምሁራኑ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ሁለቱ ሃገራት ሱዳንን በማሳተፍ ሁለቱ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ጥናት እንዲካሄደበት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ እና ግብጽ በግድቡ ላይ ያላቸው ልዩነት እየሰፋ በመጣበት ወቅት ኢትዮጵያ በሃገሪቱ በመካሄድ ላይ ካለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጀርባ ግብፅ እጇ አለበት ስትል ቅሬታን አቅርባለች።
የግብፅ ባለስልጣናት በበኩላቸው ከኢትዮጵያ በኩል የቀረበውን ቅሬታ በማስተባበል ሃገራቸው በሌላ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ሃገራት አለመግባባት ውስጥ መሆናቸውን ተከትሎ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ሁለት ግብጻውያን ባለፈው ሳምንት በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቧል። ይሁንና ኢትዮጵያም ሆነች ግብጽ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያን ሳይሰጡ ቀርተዋል።