ኅዳር ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባሕርና በረሃ አቆራርጠው በሕገወጥ መንገድ ወደ የመን ገብተዋል ያለቻቸውን ቁጥራቸው 150 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይኦኤም (IOM) አማካኝነት ወደ ትውልድ አገራቸው መላካቸውን የመን አስታውቃለች።
በቀይ ባህር ዳርቻ በምትገኘው የወደብ ከተማዋ ሁዴዳ እስር ቤት ውስጥ ከሚገኙት እስረኞች መካከል 150 በጎ ፈቃደኛ ተመላሽ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ከአይኦኤም ጋር በመተባበር ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን እሁድ እለት የየመን የስደተኞች ባለስልጣናት ገልጸዋል። ኢትዮጵያዊያን አሁንም ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በእርስበርስ ጦርነት ወደምትታመሰው የመን ከሚሰደዱ ስደተኛ ዜጎች ውስጥ አብላጫውን ቁጥር እንደሚወስዱ ሳባ የየመን የዜና አውታር ዘግቧል።