የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ ከ 11ሺ ሰው በላይ መታሰሩ ተገለጸ

ኢሳት (ህዳር 2 ፥ 2009)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ ከ11,000 ሰዎች በላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዋጁ አስፈፃሚ መርማሪ ቦርድን በመጥቀስ የስርዓቱ መገናኛ ብዙሃን አርብ ዘግበዋል።

ቦርዱ ይፋ እንዳደረገው በስድስት የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ማጎሪያ ጣቢያዎች 11 ሺህ 607 ሰዎች በቁጥጥር ስር ቢገኙም ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ አካላት የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ቁጥሩ ከዚህ እጅግ ሊበልጥ እንደሚችል በመግለጽ ላይ ናቸው።

ረቡዕ በአውሮፓ ፓርላማ ማብራሪያ የሰጡት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመበር ዶ/ር መራራ ጉዲና ከ60,000 ሰዎች በላይ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ መግለፃቸው ይታወቃል።

የአዋጁ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ የተባለው አካል ይፋ እንዳደረገው በሸዋ፣ ጦላይ፣ በዝዋይ አላጌ፣ በዲላና ይርጋለም፣ በባህር ዳር እንዲሁም በአዲስ አበባ በሚገኙ የማጎሪያ ጣቢያዎች በድምሩ 11607 ሰዎች ይገኛሉ ብሏል።

ቦርዱ ታሳሪዎቹ የተጠረጠሩበትን ጉዳይ እንዳብራራው ሁከት በመፍጠር፣ ንብረት በማውደም፣ የጸጥታ ሃይሎች ላይ ጥቃት በማድረስ፣ ሰንደቅ አላማን በማቃጠልና የአሸባሪ ድርጅቶችን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ የሚሉ ይገኙበታል።

የታሳሪዎቹ ስም ዝርዝርም በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ቦርዱ ገልጿል።

የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ከዚህ በፊት በነበሩ ህዝባዊ አመጾች ምክንያት የተገደሉና የታሰሩ ሰዎችን ቁጥር እጅግ እየቀነሰ ሪፖርት እንደሚያወጣ ከዚህ በፊት ይወጡ የነበሩ መግለጫዎች ማሳያ ናቸው።

በመስከረም ወር በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ቁጥራቸው በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች የመንግስት ታጣቂዎች በህዝቡ ላይ ጥይትና አስለቃሽ ጋዝ በመተኮሳቸው በተፈጠረው መተፋፈግና እንዲሁም ከታጣቂዎቹ  በተተኮሰ ጥይት ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

መንግስት በኢሬቻ በዓል ላይ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 55 ብቻ እንደሆነ እስካሁን ደጋግሞ እየገለፀ ቢሆንም የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ቁጥሩን ከ600 በላይ ያደርሱታል በአውሮፓ ፓርላማ ረቡዕ ማብራሪያ የሰጡት ዶ/ር መረራ ጉዲና ላለፈው አንድ ዓመት በተካሄደው ተቃውሞ የመንግስት ታጣቂዎች እስከ 1500 ሰዎች ሲገድሉ ወደ 60000 የሚጠጉ ደግሞ ለእስር ተደርገዋል።