ኢሳት (ህዳር 2 ፥ 2009)
የብሪታኒያ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቃሊቲ ታስረው ከሚገኙት ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር የነበራቸው ግንኙነት መቋረጡን ሪፕሪቭ የተሰኘ የብሪታኒያ ተቋም አስታወቀ።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከሁለት ሳምንት በፊት በወህኒ ቤት በተፈጠረ አለመግባባት ለህይወታቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ እንደሚገኙ ይኸው ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚከራከረው ድርጅት የእንግሊዝ ዲፕሎማቶች ዋቢ በማድረግ ገልጿል።
የብሪታንያ ኮሱላር ቢሮ ባለፉት ሁለት ሳምንታት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለማግኘት ሙከራ ቢያደርግም፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ አለመቻሉን ገልጿል።
እኤአ በ2014 በህገወጥ መንገድ ከየመን አየር ማረፊያ በግዳጅ ተጠልፈው ወደ ኢትዮጵያ የተወሰዱት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ከመታሰራቸው 5 አመት ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በሌሉበት የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸው ይታወሳል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከተያዙ በኋላ ለአንድ አመት ያህል በአንድ ክፍል ብቻቸውን ታስረው እንደነበር የገለጸው ሪፕሪቭ፣ ከአንድ አመት በኋላ ግን የብሪታኒያ ዲፕሎማቶች ለተወሰነ ጊዜ እንዲያገኟቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ፈቅደው እንደነበር ገልጿል።
የብሪታኒያ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲለቀቁ እስካሁን አለመጠየቁን የገለጸው ሪፕሪቭ፣ ሆኖም በወህኒ ቤት ረብሻ መፈጠሩን ተከትሎ የት እንደደረሱ አለመታወቁን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የህግ ምክር አገልግሎት እንዲያገኙ እንፈቅዳለን ቢሉም እስካሁን ድረስ ግን ቃላቸውን አለማክበራቸውን ሪፕሪቭ ገልጿል።
ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታት ጥረት እያደረገ ያለው ሪፕሪቭ የኢትዮጵያ መንግስት በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የተላለፈው የሞት ቅጣት የሚቀይርበት ምንም መንገድ አይኖርም ሲል በድረገጹ ላይ ባሰፈረው መግለጫ አስታውቋል።
ሪፕሪቭ የተባለው የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሃገሪቱ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ያሉበትን ሁኔታ ተከታትሎ በአስቸኳይ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።