ኢሳት (ህዳር 1 ፥ 2009)
የብሪታኒያ መንግስት በኢትዮጵያ በሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ መነሳቱ ይፋ ቢደረግም፣ በማንኛውም ሰዓት ተጨማሪ ክልከላዎች ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚችል አስታወቀ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መደረግን ተከትሎ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሃገራት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ከ 40 ኪሎሜትር በላይ ርቀው መሄድ ከፈለጉ ጉዳዩ ከሚመለከተው ክፍል ማሳወቅ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ መውጣቱ ይታወሳል።
የአሜሪካ መንግስትን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረትና የተለያዩ ሃገራት የተጣለው እገዳ በዕለት ስራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ሲገልፅ ቆይተዋል።
በተያዘው ሳምንት መንግስት እገዳው እንደተነሳ ማሳወቁ የሚታወስ ሲሆን፣ በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫን ያወጣው የብሪታኒያ መንግስት በዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ መነሳቱ ይፋ ቢደረግም፣ በማንኛውም ሰዓትና በአጭር ጊዜ በሚሰጥ ማሳሰቢያ ተጨማሪ ክልከላ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችል ገልጿል።
ለሃገሪቱ ዜጎች ባሰራጨው የጉዞ ማሳሰቢያ የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሃገሪቱ በማንኛውም ወቅት ሊጣል ይችላል ያለው ክልከላ በአንዳንድ አካባቢዎች በሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ተፅዕኖን ሊያሳድሩ እንደሚችል ስጋቱን አስቀምጧል።
የአዋጁን መውጣት ተከትሎ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሃገሪቱ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ ያሳሰበ ሲሆን፣ እርምጃው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ቅሬታን ፈጥሯል።
አሜሪካ የወሰደችው ዕርምጃ ተገቢ ያልሆነና የሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያሰገባ ነው ሲል መንግስት ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።
የብሪታኒያ መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎች በተለያዩ ቦታዎች በሚደረጉ እንቅስቃሴ ላይ ጥንቃቄ እንዳይለያቸው በድጋሚ አሳስቧል።
ለአስቸኳይ ስራ ካልሆነ በስተቀር ወደ አማራና የተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ዜጎቹ ጉዞን እንዳያደርጉ የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አክሎ ጥሪውን አቅርቧል።