ኢሳት (ህዳር 1 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ተደርጎ ቢገኝም፣ በሃገሪቱ ፖለቲካዊ ውጥረትና የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለጠ።
ለአንድ አመት ያህል በተለያዩ ክልሎች ሲካሄድ ከነበረው ከዚሁ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በንፁሃን ሰዎች ላይ የተፈጸመን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአስቸኳይ ማጣራት እንደሚያስፈልግም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ ለኢትዮጵያ መንግስት ባቀረበው ጥሪ አመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የጅምላ እስራት እና በጸጥታ ሃይሎች የሚፈጸመው የሃይል ዕርምጃ መቀጠሉ እጅጉን አሳሳቢ ሆኖ ይገኛል ሲሉ የድርጅቱ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ የሆኑት ሚቼሌ ካጋሪ አስታውቀዋል።
በስልጣን ላይ ያለው ገዥው የኢህአዴግ መንግስት ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሎ በተደጋጋሚ ከመግለጽ ይልቅ ሃሳባቸውን በነጻነት ሲገልፅ ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን በአስቸኳይ መልቀቅ እንዳለበት ተወካዮዋ ጥሪን አቅርበዋል።
በወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ሪፖርቱን ያወጣው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ሲካሄዱ ከቆዩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ጋር በተገናኘ በትንሹ ወደ 800 የሚሆኑ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ገልጿል።
ህዝባዊ ተቃውሞን ለመቆጣጠር በሃገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ቢደረግም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ፖለቲካዊ አለመረጋገቱ አሁንም ድረስ ሰፍኖ መቀጠሉ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አክሎ አመልክቷል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ በሃገሪቱ ለአንድ አመት ሲካሄድ ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ወደ 1ሺ 500 ሰዎች እንደተገደሉ ረቡዕ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በርካታ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተለያዩ አካላት ሲገልፅ የቆየው የሟቾች ቁጥር በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት ጥሪን ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን፣ መንግስት ለማጣራቱ ሂደት ተባባሪ እንደማይሆን ምላሽን ሰጥቷል።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅና የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ የሆኑት ሚቼሌ ካጋሪ በሃገሪቱ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ዕልባት የማይሰጠው ከሆነ ህዝባዊ ተቃውሞ ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል በአጽንዖት አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የልማት አጋር የሆኑት ሃገራትና አለም አቀፍ ተቋማት መንግስት ችግሩን ለመቆጣጠር ተግባራዊ ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰብዓዊ ጥሰቱን ያባብሰዋል ሲሉ ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።