ጥቅምት ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል የህወሃት/ ኢህአዴግን አገዛዝ በመሳሪያ ሃይል ለመታገል ወደ ጫካ የወጡ የነጻነት ሃይሎች በየጊዜው ከመንግስት ወታደሮች ጋር እየተታኮሱ ሲሆን፣ ትናንት በወገራ ወረዳ እንቃሽ በሚባለው አካባቢ የተደረገው ጦርነት ዛሬም ቀጥሎ መዋሉንና በርካታ የመንግስት ታጣቂ ሃይሎች መገደላቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመልክቷል። የተወሰነ የመንግስት ታጣቂዎች አስከሬን ጎንደር ከተማ ገብቷል። የነጻነት ሃይሎች እንደሚሉት ምንም አይነት ልምድ የሌላቸውን የአርሶአደር ታጣቂዎች በገንዘብ በመግዛት ፊት በማሰለፍ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስባቸው ተደርጓል። የመንግስት ታጣቂ አርሶአደሮች ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው በሁዋላ፣ ወታደሮች በሶስት ኦራል መኪኖች ቢደርሱም የነጻነት ሃይሎችን ጥቃት መቋቋም ሳይችሉ ቀርተዋል። የነጻነት ሃይሎች ከ40 ያላነሱ ሚሊሺዎችንና ሽምቆችን መግደላቸውን ቢገልጹም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው የተገደሉት ሚለሺያዎች እና ወታደሮች ቁጥር 30 ይደርሳል ይላሉ።
ትክክለኛውን አሃዝ ለማወቅ ያደርገነው ጥረት አልተሳካም። የአካባቢው ገዢዎች በበከሉላቸው 2 አሸባሪዎች ተገድለው 2 ደግሞ መማረካቸውን እየገለጹ ነው። ትናንት በአከር ወረዳ ልዩ ስሙ እጣን አምኒ እና ገውለል በሚባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድ የዋለ ሲሆን፣ በመንግስት ሃይሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
ከትናንት ጀምሮ በቀጠለው ውጊያ ከ2 ያላነሱ የነጻነት ሃይሎች መሰዋታቸውን ከስፍራው የሚደርሱን መረጃዎች ያመለከታሉ።በነጻነት ሃይሎች በኩል 2 መሞታቸውን ትክክል መሆኑን የሚገልጹት ተዋጊዮች፣ ከገዢው ፓርቲ ታጣቂዎች ጋር ሲነጻጸር በእነሱ ላይ የደረሰው ጉዳት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ባለፈው ቅዳሜ የስልጠና ጊዜያቸውን ያላጠናቀቁ ወታደሮች ከብር ሸለቆ ተነስተው ወደ ሰሜን ጎንደር እንዲጓዙ ተደርጓል። ሰልጣኞች የ3 ወራት የውትድርና ስልጠናቸውን ሳያጠናቅቁ በሁለተኛ ወራቸው ለግዳጅ እንዲሰማሩ ተደርጓል። በእንቃሽ የሚካሄደው ውጊያ ከእነዚህ አዲስ ሰልጣኞች ጋር ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም።
በሌላ በኩል በመከላከያ ሰራዊት ደህንነትና በዋናው የአገሪቱ ደህንነት መካከል ያለው አለመግባባት እየሰፋ መምጣቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። መስከረም 1 ቀን 2009 ዓም ኮተቤ አካባቢ በሚገኘው ሚስጢራዊ የደህነት ግቢ ውስጥ በደህንነቶች መካከል በተነሳ አለመግባባት ከሌሊቱ 10 ሰአት እስከ ሌሊቱ 11፡45 የተኩስ ለውውጥ የተደረገ ሲሆን፣ በዚህ የተኩስ ለውውጥ ብርሃን ወልደየስ የተባለ ከፍተኛ የህወሃት ነባር የመረጃ ሰውና የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጥበቃ ልዩ ሃይል አስተባባሪ ሳይገደል እንዳልቀረ ምንጮች ገልጸዋል።
በብሄራዊ የደህንነት መስሪያ ቤትና በመከላከያ የደህንነት ተቋም መካከል ያለው አለመግባባት መስፋቱን ተከትሎ፣ በውጭ የሚገኙ አንዳንድ የደህንነት አባላት በቀጥታ ለመከላከያ ደህንነት ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘዋል። የመከላከያ የደህንነት ኤጀንሲ ልምድ ያላቸው የደህንነት ሰራተኞች የሌሉት ቢሆንም፣ በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት በኩል የሚመጣውን መረጃ አልቀበልም ከማለት አልፎ የውጭ አገር የስለላ ሰራተኞችን እያፈላለገ ፣ በቀጥታ ለመከላከያ ደህንነት ሪፖርት እንዲያደርጉ እያዘዘ ነው።
በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለው አለመግባባት እየሰፋ ቢመጣም፣ ያለመግባባቱ መንስኤ ምን እንደሆነ ለማውቅ አልተቻለም። አንዳንድ የደህንነት ሰራተኞች እንደሚሉት ከሆነ የብሄራዊ ደህንነት ተቋሙ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችን መሰለል መጀመሩ ለክፍፍሉ መንስኤ ሆኗል።