ኢሳት (ጥቅምት 30 ፥ 2009)
የአውሮፓ ህብረት በወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ረቡዕ ዋና መቀመጫ በሚገኝበት የብራሰልሷ መዲና ብራሰልስ ልዩ ሪፖርትን የማድመጥ መድረክ አካሄደ።
በዚሁ መድረክ የግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የኦሮሞ ፊዴራሊስት ኮንግሬስ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ እንዲሁም አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በአካል በመገኘት በህብረቱ አባላትና አመራሮች ማብራሪያን ሰጥተዋል።
በመድረኩ ማብራሪያን ያቀረቡት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ በኢትዮጵያ ያለው አለመረጋጋት ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ እና የከፋ ቀውስ ከማስከተሉ በፊት ምዕራባውያን ሃገራት አፋጣኝ እርምጃን መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ባለፈው አመት ተመሳሳይ ማብራሪያን አቅርበው የነበሩት የግንቦት 7 ሊቀመንበር በሃገሪቱ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲያካሄዱ የነበሩት የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ያሳዩት ህብረትና አንድነት መንግስትን ጭንቀት ውስጥ ከቶት እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ግድያና አፈና እንደብቸኛ አማራጭ አድርጎ ወስዷል ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ምዕራባውያን ሃገራት ከኢትዮጵያ ጋር በሽብርተኛ ጉዳይ ያላቸውን አጋርነት በማስቀደም ለወቅታዊ የሃገሪቱ ችግሮች በቂ ትኩረት አለመስጠታቸው ራሳቸውን ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችልም አስረድተዋል።
በሃገሪቱ ያለውን ፖለቲካዊ ውጥረት ዕልባት ለመስጠት በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚያካትት የሽግግር ምክር ቤት ማቋቋሙ ዋነኛው መፍትሄ መሆኑንን ገልጸዋል።
በአውሮፓ ህብረት መቀመጫ በሚገኝበት ብራሰልስ ከተማ ተገኝተው በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያን ያቀረቡት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳና፣ የፖለቲካና የህሊና ዕስረኞችን በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጥሪን አቅርበዋል።
ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ጥሪውን ተቀብሎ ዕርምጃዎችን የማይወስድ ከሆነም፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በጀመረው መንገድ ራሱን ነጻ ያወጣል ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
መንግስት ለቀረበው ጥያቄ በጎ ምላሽን የማይሰጥ ከሆነ በግላቸው የሚወስዱት ዕርምጃ እንዳለ ጥያቄ የቀረበላቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ “ አገዛዙን እስከ መጨረሻዋ እስትንፋሴ እፋለመዋለሁ” ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።
በዚሁ መድረክ ተጋባዥ ተሳታፊ የነበሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በአማራ ክሎች ሲካሄዱ በቆዩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ወደ 1ሺ 500 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ገዢው መንግስት እየወሰደ ባለው በዚሁ የሃይል እርምጃ ተጨማሪ ወደ 60ሺ አካባቢ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንም የኦፌኮ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።
ሁለቱ ክልሎች በአሁኑ ወቅት በወታደራዊ አገዛዝ ስር ይገኛሉ ያሉት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአስቸኳይ እንዲነሳና አዲስ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጥሪን አቅርበዋል።
አትሌት ፈይሳ ለሊሳ በበኩሉ የአውሮፓ ህብረት አምባገነን ሲል ለገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍን ከማድረግ እንዲቆጠብ ጥሪውን አቅርቧል።