የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሁኔታ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ የብሪታኒያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ጠየቁ

ኢሳት (ጥቅምት 29 ፥ 2009)

የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የሃገሪቱ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ያሉበትን ሁኔታ ተከታትሎ ለህዝብ በአስቸኳይ ይፋ እንዲያደርግ በድጋሚ ጥሪን አቀረቡ።

የአቶ አንዳርጋቸው ቤተሰቦች በብሪታኒያ ባለስልጣናት በኩል አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደማይገኙ መረጃን ቢሰጡም የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ማረጋገጫ አለማግኘቱን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ከነሃሴ ወር ጀምሮ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን የመጎብኘት እድል እንዳልነበረ ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የመረጃውን መውጣት ተከትሎ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ወክሎ የሚገኘው ሪፕሪቭ የተሰኘው አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት በብሪታኒያ መንግስት ላይ ግፊት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ኢክሌሲያ የተሰኘ መጽሄት ማክሰኞች ዘግቧል።

በቃሊቲ ታስረው የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ህይወታቸው አደጋ ውስጥ ስለመሆኑ የብሪታኒያ ባለስልጣናት ከቀናት በፊት ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

በብሪታኒያ መንግስት ላይ ግፊትን እያደረጉ ያሉ የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስስቴር የዜጋውን የደህንነት ሁኔታ በአስቸኳይ በማጣራት ለቤተሰቦቻቸው መግለጽ እንደሚገባው አሳስበዋል።

የብሪታኒያ ዲፕሎማቶች አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ያሉበት እስር ቤት ውስጥ በቅርቡ ተፈጥሯል ከተባለ ሁከት ጋር በተገናኘ አቶ አንዳርጋቸው ያደረባቸውን ስጋት እንደገለጹ ለቤተሰቦቻቸው መረጃ መስጠታቸው ታውቋል።

ሪፕሪቭ የተሰኘ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የብሪታኒያ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የህግ ምክር እንዲያገኙ እያቀረበ ያለውን ጥያቄ በመተው ወደ ብሪታኒያ የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት ጥሪን አቅርቧል።

የብሪታኒያ ፓርላማ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይን ልዩ ትኩረት በመስጠት በመከታተል ላይ እንደሚገኝም መጽሄቱ በዘገባው አስፍሯል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ያሉበት እስር ቤት ውስጥ ተፈጥሯል ሰለተባለው ሁከት ከኢትዮጵያ በኩል የተሰጠ ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ድርጊቱ በሁለቱ ሃገራት መካከል በአዲስ መልክ መነጋገሪያ መሆኑ ታውቋል።