ኢሳት (ጥቅምት 28 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የሚገኙ የደቡብ ሱዳን ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሃገራቸው መንግስት ሊሰጠን የሚገባውን ጥቅማጥቅም አዘግይቶብናል በሚል በአዲስ አበባ በሚገኘው የደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ላይ ወረራን ፈጸሙ።
ተማሪዎቹ በሃገራቸው ኤምባሲ ላይ የፈጸሙትን ወረራ ለማክሸፍ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ ወደ 42 የሚደርሱ ተማሪዎች ለእስር መዳረጋቸው ታውቋል።
ስሙን መግለጽ ያልፈለገ የተማሪዎች ተወካይ ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውንና የኤምባሲው ሰራተኞች የሃይል ዕርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ታማዙጂ ለተሰኘ የደቡብ ሱዳን ራድዮ ጣቢያ አስታውቋል።
ተቃውሞን ያቀረቡት ተማሪዎች በየወሩ ሲሰጣቸው የነበረ 100 የአሜሪካ ዶላር ለአራት አራት ወር ያህል ጊዜ እንዳልተከፈላቸው ይገልጻሉ።
ለተማሪዎቹ የምግብ አገልግሎት የሚያቀርብ አንድ ድርጅት 14 ሺ ዶላር ክፍያ ሳይፈጸምለት መቆየቱንም የራዲዮ ጣቢያው ዘግቧል።
የተለያዩ የሙያ ስልጠናን በመከታተል ላይ የሚገኙት እነዚሁ ተማሪዎች በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መንግስታት በኩል በተደረሰ ስምምነት የነጻ የትምህርት ዕድል ቢሰጣቸውም በየወሩ የሚሰጣቸው ጥቅማጥቅም ግን ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት መቋረጡን ለመገኛኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የሃገሪቱ ባለስጣናት በበኩላቸው ተማሪዎቹ ያቀረቡትን ጥያቄ እልባት ለመስጠት ጥረት እንደሚያደርጉ ምላሽን የሰጡ ሲሆን፣ ተማሪዎች ለችግር መዳረጋቸው እየገለጸ ይገኛል።
ለእስር ስለተዳረጉት 42 ተማሪዎች የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ባለፈው አመት ተማሪዎቹ ተመሳሳይ ወረራን በኢምባሲው ላይ ፈጽመው እንደነበር ታውቋል።