በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ መከሰቱ ተገለጸ

ኢሳት (ጥቅምት 28 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች አዲስ የድርቅ አደጋ መከሰቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰኞ ይፋ አደረገ።

የብሄራዊ አደጋ መከላከያ ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ በ212 ወረዳዎች ላይ ባካሄዱት የሰብል እርሻ ጥናት አዲሱ ድርቅ መከሰቱ ሊታወቅ እንደቻለ ተቋማቱ በጋራ አስታውቀዋል።

በዚሁ ጥናት ውስጥ ተካተው ከነበሩት ወረዳዎች መካከል 93 የሚሆኑን ከፍተኛ የድርቅ አደጋ እንዳጋጠማቸው ለመረዳት ተችሏል።

በኦሮሚያ ክልል 32 ወረዳዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት በቂ የሰብል ምርት ማግኘት ያልቻሉ ሲሆን፣ ተጨማሪ 21 ወረዳዎችም አማካይ የሆነ የሰብል ምርት ሊያገኙ ይቻላል ተብሎ ተገምቷል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ ክልል 15 ወረዳዎች በቂ ምርት ሊያገኙ ባለመቻላቸው ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ ሲሆን፣ 12 ወረዳዎች ዳግም ማግኘት ከሚጠበቅባቸው በታች የሰብል ምርት ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ በእነዚሁ ወረዳዎች የተከሰተው የምርት መቀነስ ማጋጠም በአካባቢው አዲስ የድርቅ አደጋ እንዲከሰት ማድረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

ከአንድ አመት በፊት በስድስት ክልሎች ተከስቶ በነበረው የድርቅ አደጋ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ መጋለጣቸው ይታወሳል።

ይሁንና ችግሩ ዕልባት ባለማግኘቱ ምክንያት አሁንም ድረስ 9.7 ሚሊዮን ሰዎች ለምግብ ዕርዳታ ተጋልጠው እንደሚገኙ ተመድ ገልጿል።

በደቡባዊ ምስራቅ በአዲስ መልክ የተከሰተው የድርቅ አደጋ የተረጂዎችን ቁጥር ከፍ ያደርገዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ እስከ ቀጣዩ አመት ድረስ ሊዘልቅ ይችላል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ ይፋ አድርጓል።