ኢሳት (ጥቅምት 25 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ቁጥርና የደህንነት ሁኔታ ግልጽ እንዲደረገ ተጠየቀ።
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች እየተካሄደ ባለው የእስር ዘመቻ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማትን ጨምሮ በርካታ መንግስታዊ ድርጅቶች ወደ እስር ቤት መለወጣቸውን ነዋሪዎች አስታውቀዋል።
ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊነት የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት ለእስር የተዳረጉ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥርና የደህንነት ሁኔታ ለህዝብ ይፋ አለማድረጉ ስጋት እየፈጠረ መምጣቱን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች አስረድተዋል።
የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ በበኩላቸው በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች አያያዝ አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ግልጽ ይደረጋል ሲሉ አርብ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይሁንና ሚኒስትሩ መረጃውን መቼ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ በዘመቻው ለእስር ስለተዳረጉ ሰዎች ቁጥርም ማብራሪያን ሳይሰጡ ቀርተዋል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በማባባስ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች እስራት ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ።
በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት ለጊዜያዊ እስር ቤት ውለው እንደሚገኙም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ እስካሁን ያለውን የተጠርጣሪዎች አያያዝ የምርመራ ውጤት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ሲል ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቋል።
የአዋጁን መውጣት ተከትሎ የጸጥታ ሃይሎች ማንኛውንም ተጠርጣሪ ግለሰብ በቁጥጥር ስር የማዋልና ምርመራን የማካሄድ ስልጣን የተሰጣቸው ሲሆን፣ ተጠርጣሪዎችንም ያሉበትን ቦታ እንዲያሳውቁ በአዋጁ ተደንግጓል።