ኢሳት (ጥቅምት 24 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ውስጥ የቀጠለው ህዝባዊ ዕምቢተኝነትና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ እንዲመሰረት ምክንያት መሆኑን ድርጅቱ አስታወቀ።
ባለፈው ዕሁድ በይፋ መመስረቱ የተገለጸው የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አሁን የተፈጠረው ህብረት ሃገር ቤት እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ዕምቢተኝነት የወለደው ጭምር በመሆኑ እስከዛሬው የተለየ መሆኑን አመልክተዋል።
የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያው ግንባር፣ አርበኞች ግንቦት 7, የአፋር ፓርቲ እንዲሁም የሲዳማ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በጋራ የመሰረቱትና የአማራ ህዝብ ተወካይ የተሳተፉበት ይህ የጋራ ንቅናቄ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ቡድን በስልጣን ላይ እንደማይቆይ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጭምር ግንዛቤ ማግኘቱን ተከትሎ ዕውን መሆኑንና አማራጭ ሆኖ መምጣቱን አስረድተዋል።
በሃገራዊ ንቅናቄን ም/ቤት በሊቀመንበርነት የሚመሩት አቶ ሌንጮ ለታና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ መሆናቸውም ተመልክቷል። የንቅናቄው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን በሊቀመንበርነት የሚመሩት ዶ/ር ዲማ ነገዎ ከሌሎቹ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በጋራ ለኢሳት በሰጡት ቃለ-ምልልስ ሃገራችንን ከውድቀት ህዝባችንን ከውርደት የምናድነበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ሲሉም ተደምጠዋል።
ሃገራዊ ንቅናቄው ስ/አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ዶ/ር ዲማ ነገዎና ሌሎች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አቶ ሙሉነህ እዩኤል ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ እንዲሁም አቶ በቀለ ዋዮ እና አቶ ሃይለ-ገብርዔል አያሌው ከኢሳት ጋር ያደረጉትን ቃለ-ምልልስ በኢሳት ቴለቪዥን እና ሬዲዮ ይቀርባል።