ኢሳት (ጥቅምት 23 ፥ 2009)
በባህርዳር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ የነዋሪዎችና የነጋዴዎችን መታሰር በመቃወም የከተማዋ ወጣቶች ቦንብ ማፈንዳታቸውን ተነገረ።
ወጣቶቹ እርምጃውን የወሰዱት ቀበሌ 03 በሚገኘው የአቶ ገለታ እና አቶ ስለሺ በተባሉ የብአዴን ባለስልጣናት መኖሪያ ቤቶች ግቢ ውስጥ ነው።
ኪቤአድ ግቢ አካቢቢና በባህር ዳር ማዘጋጃ ዙሪያ የተጣሉት ቦምቦች ስላደረሱት ጉዳት የተባለ ነገር የለም። ይህ በእንዲህ እንዳለም በጢስ አባይ ከተማ የጎበዝ አለቃ በመሆን የህዝቡን እምቢተኝነት ሲመራ የነበረው ምክሩ ብርሃኑ እና ሌሎች ሶስት ተማሪዎች በታጠቁ የስርዓቱ ወታደሮች ተገድለዋል።
ጥቃቱ በተከፈተበት ጊዜ 4 ሰዎች ከመገደላቸው ሌላ ደሴ ታደሰ የተባለ የጎበዝ አለቃ በስርዓቱ ታጣቂዎች ታፍኖ መወሰዱንም ዕማኞች ለኢሳት ተናግረዋል። ጢስ አባይ በተኩስ ስትናጥ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ ዜና በባህርዳር መደብሮቻችሁን በአድማ ወቅት ዘግታችኋል የተባሉ ነጋዴዎች ፍ/ቤት በቀረቡበት ጊዜ በችሎቱ የተገኙት በርካታ ቤተሰቦችና የከተማ ነዋሪዎች በስርዓቱ ታጣቂዎች ታግተው መዋላቸው ተነግሯል።
በህወሃት ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የህዝብ ተቃውሞን ለማብረድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያውጅም፣ ህብረተሰቡ ትግሉን አለማቆሙን ታዛቢዎች ይናገራሉ።