በ“ቀይ ዞን” በሚገኙ አካባቢዎች የእርዳታ አሰጣጥ ሂደትን የሚጠይቅ ጥያቄ ለኮማንድ ፖስት ቀረበ

ኢሳት (ጥቅምት 23 ፥ 2009)

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “ቀይ ዞን” ተብለው በኮማንድ ፖስት በታወጁ አካባቢዎች ለሚገኙ የድርቅ ተረጂዎች የእርዳታ አሰጣጥ ሂደትን የሚጠይቅ ጥያቄ ለመንግስት መቅረቡ ተገለጸ። ማብራሪያውን የጠየቀው የኢትዮጵያ የስብዓዊ ዕርዳታ ቡድን  እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ ቡድን ከተባበሩት መንግስታት፣ ቀይ መስቀል/ጨረቃ ማህበር፣ ለጋሽ ድርጅቶችና አለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮችን ያካተተ ነው ተብሏል።

የዕርዳታ ስትራቴጂና ስርጭትን የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ ቡድን በድርቅ ለተጎዱ የ 9.7 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና 760ሺ የሚጠጉ የጎረቤት አገር ስደተኞችን እርዳታ የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል። አብዛኞቹ ተረጂዎች መንግስት ቀይ ዞን ብሎ በፈረጃቸው አካባቢዎች የሚገኙ መሆናቸውን ፎርቹን የተባለው በኢትዮጵያ የሚታተመው ጋዜጣ ዘግቧል።

በእርዳታ አሰጣጥ ሂደት ዙሪያ ከኮማንድ ፖስት ማብራሪያ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ድርጅቶቹ ዕርዳታ በሚያከፈፍሉበት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብዙ ሰው መሰብሰብ ስለሚከለክል እንደሆነ ያስረዱት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ተወካይ፣ መንግስት ቀይ ዞን ብሎ በሚጠራው ክልል ሰዎች በርከት ብለው ከተሰበሰቡ ኮማንድ ፖስቱ ምን አይነት እርምጃ እንደሚወስድ አለመታወቁ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ዕርዳታ ስናከፋፈል ብዛት ያለው ሰው መሰብሰቡ አይቀርም ያሉት እኚሁ ስማቸው ያለተገለጸው የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ተወካይ፣ መንግስት ይህንን ሁኔታ ግልጽነት በተመላበት ሁኔታ ሊያብራራና ሊያስረዳን ይገባል ሲሉ መናገራቸው ተመልክቷል።

በኮማንድ ፖስቱ ቀይ ዞን ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በአገሪቷ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ የሆነ ሲሆን፣ በ 9 ዋና ዋና መንገዶች ማለትም ከአዲስ አበባ ጅቡቲ፣ ከአዲስ አበባ ሻሸማኔ፣ ከአዲስ አበባ ሃረር፣ ከአዲስ አበባ አሶሳ፣ ከአዲስ አበባ ጋምቤላ፣ ከአዲስ አበባ ገብረ ጉራቻ፣ ሻሸማኔ ሞያሌ፣ ጎንደር መተማ እና ጎንደር ሁመራ ያለውን መንገድ የሚያጠቃልል ነው።

ኮማንድ ፖስቱ ቀይ ዞን ብሎ በፈረጃቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተረጂዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ በአስቸኳይ የሚፈልጉ መሆናቸውን የገለጸው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ ቡድን፣ በምስራቅ ትግራይ፣ በአፋር፣ እና በኦሮሚያ ቦረና አካባቢዎች ከፍተኛ ድርቅ ያጋጠማቸው እንደሆነ በዚሁ በፎርቹን ጋዜጣ የወጣው ዘገባ ያስረዳል።

ዕሁድ መስከረም 29, 2009 ይፋ የሆነውና ከመስከረም 28 ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑ የተገለፀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በመላዋ ኢትዮጵያ ስራ ላይ መዋሉ ይታወቃል።

ኢትዮጵያውያን በምልክት ቋንቋ መነጋገርን ወይንም ምልክት ማሳየትን ጨምሮ በሚናገሩት ብቻ ሳይሆን በሚያዩትና በሚሰሙት ነገር ላይ ጭምር ገደብ የጣለው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአዲስ አበባ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ከአዲስ አበባ ከ40 ኪ/ሜትር የበለጠ መንገድ ለመጓዝ ከፈለጉ ለኮማንድ ፖስቱ ማሳወቅ ግዴታቸው መሆኑንም ማስቀመጡን መዘገባችን አይዘነጋም።