ጥቅምት ፳፩ (ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት የወታደራዊ የደህንነት ምንጮች እንደገለጹት በሶማሊያ በአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ስም ያልታቀፉትና ላለፉት 4 አመታት ከአልሸባብ ጋር ሲዋጉ ከነበሩት ወታደሮች መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩት ትእዛዝ አንቀበልም በማለት አምጸው ከቀዩ በሁዋላ ከ70 ያላናሱት የጦር መሳሪያዎቻቸውን ሸጠው ባህር ተሻግረው ወደ አረብ አገራት ሰያቀኑ፣ ቀሪዎቹ ወደ አገሩ ከተመለሰው ጦር ጋር አብረን አንጓዝም በማለት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መበታተናቸውን ገልጸዋል።
አመጹ ለወራት የዘለቀ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ ወታደሮች ከሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች መካከል ዘረኝነትና የክፍያ መቋረጥ ዋነኞቹ ናቸው። በአመጹ ውስጥ የተሳተፉት ወደ ኢትዮጵያ እንደመለሱ ለማግባባት ሙከራ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ወደ አገራቸው ሲመለሱ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው በመግለጽ ማግባባቱን ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
ወታደራዊ የደህንነት ምንጮች እንደሚሉት ወታደሮች ትእዛዝ አንቀበልም ማለታቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪም ሆነ የመከላከያ ሚኒስቴር ለ3 ወራት ደሞዝ ሳይከፍሉ ቆይተዋል። በሶማሊያ ውስጥ ሁለት አይነት የኢትዮጵያ ጦር ያለ ሲሆን፣ አንደኛው ጦር በአፍሪካ ሰላም አስካበሪ ( አሚሶም ) ስር የሚገኘውና በዶላር ክፍያ የሚያገኘው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ይህን ሃይል ይጠብቃል ተብሎ ያለ አሚሶም እውቅና ሶማሊያ የተላከው ከ4 ሺ በላይ ጦር ነው። አሚሶም በስሩ ላለው የኢትዮጵያ ጦር ትእዛዝ ሲያስተላልፍ፣ የኢትዮጵያ ጦር በፈንታው ትእዛዙን በአሚሶም ስር ላልታፈቀው ጦር አስተላልፎ የተለያዩ ጥቃቶች ሲፈጸሙ የቆዩ ሲሆን፣ ካለፉት 4 ወራት ጀምሮ ግን ይህ ጦር እኛ በቂ ደሞዝ ሳይከፈለን የእነሱን ስራ መስራት አንችልም የሚል ጠንካራ አቋም በመያዙ፣ አሚሶም ለኢትዮጵያ ወታደሮች የሶስት ወራት ደሞዝ ሳይከፍል ቆይቷል። መከላከያ ሚኒስቴርም በወታደሮች አመጽ በመበሳጨት የ3 ወራት ደሞዝ ያልከፈለ ሲሆን፣ በመጨረሻም 4 ሺ የሚሆነውን ወታደር ከሶማሊያ ለማስወጣት ተገዷል። ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ ውስጥ ቤተሰብ የመሰሩትና በአብዛኛው የአንድ ብሄር ተወላጆች የሆኑት በብዛት ሲመለሱ በአመጹ የተሳተፉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ትእዛዙን ባለመቀበል ሳይመለሱ ቀርተዋል።
አንዳንድ ወታደሮች የተሳፈሩበትን መኪና መሃል መንገድ ላይ እያቆሙ መጥፋታቸውንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል። በሌላ በኩል ወሳኝ የሚባሉ የደህንነት አባላት መገደላቸው እንዲሁም ሶማሊላንድ በኢትዮጵያ ላይ ፊቷን ማዞሩዋ ሶማሊያ በሚገኘው ጦር ላይ ተጨማሪ ችግር ሲፈጥር መቆየቱን ምንጮች ገልጸዋል። አብዛኛው የደህንነት ስራ የሚቀነባበረው ሶማሊላንድ ውስጥ ሲሆን፣ ሶማሊላንድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ላይ ፊቷን አዙራለች። ሶማሊላንድ የኢትዮጵያ ወታደራዊ የደህንነት አባላት ከአገሩዋ እንዲወጡ መጠየቋም ታውቋል።
“የአንድ ብሄር አባላት ብቻ ሶማሊላንድ ይመደባሉ፣ ይህ ችግር እየፈጠረ ነው” በሚል ቅሬታ ያቀረበው የሶማሊላንድ መንግስት፣ ከ20 በላይ በኦነግ አባላትነት ስም የተያዙትን ኢትዮጵያውያንን ለቀዋል። ኢህአዴግ በበኩሉ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን የሶማሊላንድ መንግስት የሚቃወም የተቃዋሚ ሃይል በመደገፍ ላይ መሆኑ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበልጥ አሻክሮታል። ሶማሊላንድ እንደአገር እውቅና ባታገኝም ራሱዋን እንደአገር በመቁጠር ከተለያዩ አገራት ጋር ግንኙነት ታደርጋለች። በአሁኑ ሰአት በወኪልነት ከሚገኘው የቀድሞው የ14ኛው ክፍለጦር አዛዥ ብርጋዴር ጄ/ል በርሄ ተስፋዬ ውጭ ሁሉም የህወሃት ባለስልጣናት ከአገሪቱ ለቀዋል።
የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከአሚሶም ውጭ የሆነውን ሰራዊት ከሶማሊያ ማስወጣታቸውን ገልጸው ነበር። አቶ ጌታቸው ለጦሩ መውጣት የሰጡት ምክንያት የገንዘብ እጥረት የሚል ነበር።
በሶማሊያ ለረጅም አመታት የቆየው የአጋዚ ጦር ከወጣ በሁዋላ እየተመናመነ መምጣቱን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።