የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የቱሪዝም ዘርፍን ክፉኛ እየጎዳው እንደሆነ ተገለጸ

ኢሳት (ጥቅምት 21 ፥ 2009)

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የቱሪዝም ዘርፉን ክፉኛ እየጎዳው እንደሆነ መንግስት አስታወቀ።

ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስተር በቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ በተጠራ ስብሰባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ የቱሪስቶች ፍልሰት ክፉኛ እንደተስተጓጎለና ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ቱሪስቶች ከፍተኛ መጉላላት እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ ቱሪስቶች ከፍተኛ መጉላላት እንደደረሰባቸው ለማሳየት በአብነት ካነሷቸው ውስጥ “ቱሪስቶች ዲፕሎማት ናቸው አይደላችሁም በሚል ፍተሻ መቸገራቸው፣ ባንኮች ጉዞ ሲሰረዝ ያስገቡትን ገንዘብ የውጭ ምንዛሪ ይፈልጋል በማለት ለመመለስ ፈቃደኛ አለመሆናቸው፣ የኢንተርኔት መቆራረጥና ወይም አለመኖር በዲፕሎማት የጉዞ እቀባ ድንጋጌ ላይ ግልጸኝነት አለመኖር” የተዘረዘሩ ምክንያቶች ናቸው።

የአስጎብኚ ድርጅት ባለቤቶችና ተወካዮች በስብሰባው ላይ የተሰማቸውን ቅሬታ የገለጹ ሲሆን፣ የአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ከቀን ወደ ቀን እየተሽመደመደ መሄዱን ተናግረዋል። ቱሪስቶች በወሰዱት የጉዞ ስረዛ ምክንያት ኪሳራ እየተዳረጉ መሆኑን ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተለያዩ አለም አቀፍ አስጎብኚ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ሊልኩ ያዘጋጇቸውን ቱሪስቶች መሰረዛቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ በእንግሊዝ አገር የሚገኘውና “Sage Holidays” በመባል የሚታወቀ አስጎብኚ ድርጅት በኢትዮጵያ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ጉብኝቱ መሰረዙ ታውቋል።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ በኢንተርኔት ማህበራዊ ድረ-ገጾች በመዘጋታቸው ምክንያት ደንበኞቹ ያሰሙት ቅሬታና ስጋት እንደሚጋራና የኤምባሲው ተግባራትም እንደተስተጓጎሉ አስታውቋል። “ኢንተርኔት ሙሉ ለሙሉ መቼ እንደሚከፈት አናውቅም” በማለት የገለጸው የአሜሪካ ኤምባሲ ደንበኞቹ የሚያገኙትን የማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎውሺፕ፣ ቪዛ ሎተሪና፣ ሌሎች ፕሮግራሞች አዳጋች እንዳደረገባቸው አስታውቀዋል።

የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ለአለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት በሰጡት መግለጫ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለውጭ ባለሃብቶችና ቱሪስቶች ዋስትና እና ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ማለታቸው የሚታወስ ነው።