ኢሳት (ጥቅምት 18 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በርካታ የብሪታኒያ አስጎብኚ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ሊያደርጉ የነበረ የጉዞ ፕሮግራም ሰረዙ።
የጉብኝት ፕሮግራሞቻቸውን በመሰረዝ ላይ ያሉት እነዚሁ ድርጅቶች ለመዘገቧቸው ጎብኚዎች ክፍያን እየመለሱ እንደሆነ ቴሌግራፍ የተሰኘ የብሪታኒያ ጋዜጣ አርብ ዘግቧል።
ሳጋ፣ ኩኦኒ፣ እና ኦክስ እንዲሁም ኪንግስ የተሰኙ አስጎብኚ ድርጅቶች የጉብኝት ፕሮግራሞችን በመሰረዝ ላይ ካሉ ተቋማት መካከል ሲሆኑ ሌሎች የአውሮፓ ተመሳሳይ ተቋማትም የጉዞ ፕሮግራሞችን እየሰረዙ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።
ከቀናት በፊት ኢሳት ምንጮች ዋቢ በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ የቱሪስቶች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን መዘገቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት በበኩሉ የቱሪስቶች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን አረጋግጦ ወደ ሃገሪቱ የሚመጡ ቱሪስቶች ያለምንም እገዳ ጉብኝትን እንደሚያደርጉ መግለጹ ይታወሳል።
ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣቱን ተከትሎ መንግስት መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት ዲፕሎማቶች ከ 40 ኪሎሜትር በላይ ርቀው መሄድ ከፈለጉ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንዳለባቸው እገዳን አስቀምጧል።
ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው አዋጅ ግን ወደ ሃገሪቱ መጓዝ በሚፈልጉ ቱሪስቶችና ሌሎች አካላት ዘንድ ተፅዕኖ ማሳደሩ ይነገራል።
ይህንንም ምክንያት በማድረግ በብሪታኒያ የሚገኙ በርካታ የቱሪስት አስጎብኚ ድርጅቶች የጉብኝት ፕሮግራማቸውን በመሰረዝ ለደንበኞቻቸው አማራጭን እየሰጡ እንደሆነ ቴሌግራፍ ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።
በተያዘው ሳምንት የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎቿ በጣም አስቸኳይ ካልሆነ ጉዳይ ውጭ ወደ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች እንዳይጓዙ ማሳሰቢያ ማሰራጨቱ ይታወሳል።
የሳጋ አስጎብኚ ድርጅት የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ያወጣው የጉዞ ማሳሰቢያ የጉዞ ሰነዱን ለመሰረዝ ምክንያት መሆኑን ለጋዜጣው አስረድተዋል።
የጉዞ ፕሮግራሞቻቸውን በመሰረዝ ላይ ያሉት ድርጅቶች የፈረንጆቹ አዲስ አመት መቅረብን ምክንያት በማድረግ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጉብኝትን ለማድረግ እቅድ ይዘው እንደነበር ታውቋል።
የቱሪስቶቹ ጉዞ መሰረዝ በኢትዮጵያ የቱሪስት ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።