በሃረሬ ክልል ካደሬዎች ሰዎች ቤት በድንገት እየገቡ “ኢሳትን ታያላችሁ ወይ?” እያሉ በመጠየቅ ላይ ናቸው

ጥቅምት ፲፮ (አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የክልሉ ወኪላችን እንደገለጸው ባለፈው ሳምንት ህዝቡ ዲሽ እንዲያወርድ ማስጠንቀቂያ ከቀረበለት በሁዋላ፣ ካድሬዎች በድንገት ወደ ግለሰቦች ቤት ዘው ብለው በመግባት “ እንዴት ነው ኢሳትን ታያላችሁ?” እያሉ በመጠየቅ ላይ ናቸው።አብዛኛው ህዝብ ኢሳትን ለማየት ሌሎች አማራጮችን እየተጠቀመ ነው። ኢሳትን ከማየት ሙሉ በሙሉ የሚከለክለን ነገር የለም የሚሉት ነዋሪዎች፣ ኢሳትን ለማየት ለሚዲያ ፍጆታ የማይውሉ ሌሎች አማራጮችን እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በሃረር ህዳር 29 የሚከበረውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አስመልክቶ በክልሉ ትምህርት ቤቶችና መስሪያ ቤቶች ለ2 ሳምንታት እንደሚዘጉ ታውቋል። በሌላ በኩል 300 ሚሊዮን ብር የወጣበት እና በቻይናዎች የሚሰራው ከአመሬሳ እስከ ሃረር ስታዲየም ድረስ ያለው የመንገድ ስራ ተጠናቆ ለበአሉ ለማድረስ የሚደረገው ሩጫ እንደተጓተተ ወኪላችን ገልጿል። ለከተማዋ ማስዋቢያ በሚል 200 ሚሊዮን ብር ወጪ የሆነ ሲሆን፣ አብዛኛውን ስራ የሚሰሩት የህወሃት ባለሃብቶች ናቸው።