የቪዥን ኢትዮጵያ ወይም ራዕይ ኢትዮጵያ  ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የሽግግር ካውንስል እንዲቋቋም ጥሪ አቀረቡ።

ጥቅምት ፲፮ (አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ይህን ጥሪ ያቀረቡት ባሳለፍነው ሳምንት  በዋሽንግተን ዲሲ ቪዥን ኢትዮጵያ -ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ራዲዮ-ኢሳት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው  ኮንፈረንስ መጠናቀቁን ተከትሎ ባወጡት ባለ 11 ነጥብ የአቋም መግለጫ ነው።

በኢትዮጵያ ሕዝብ  የሚቋቋመው የሽግግር ካውንስል አዲስ ሪፐብሊክና አዲስ የአንድነት መንግስት እስኪቋቋም ድረስ ሰላማዊና የተረጋጋ የሽግግር ሁኔታ እንዲፈጠር ነገሮችን የሚያመቻች ነው።

ካውንስሉ በተባበሩት መንግስታት የሰባአዊ መብቶች ድንጋጌና  በአፍሪካ የሰብአዊ መብት ቻርተር መሰረት  የመሰብሰብን፣ የመደራጀትን፣የእምነትን፣ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመንቀሳቀስን  የፕሬስን፣ በህይወት የመኖርን ጨምሮ የሲቪክና የፖለቲካ  መብቶችን ማክበር እንዳለበት የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች አቋም መግለጫ ያመለክታል።

ካውንስሉ የአዲሱን ትውልድ የፖለቲካ መሪዎች ጨምሮ ሁሉንም ነባርና አዳዲስ  ፖለቲካ ፓርቲዎችን መጋበዝ አለባቸው ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ሕዝባዊ የመሰብሰቢያ ቦታዎች ሁሉም በሂደቱ ላይ  የተሟላ ውይይት  ማድረግ እንዳለባቸው ተስማምተዋል።

የሽግግር  ጊዜ ካውንስሉበውጪ ሀገራት ያሉ በትጥቅ ትግል የሚንቀሳቀሱና ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ  የሚያመቻችና ለደህንነታቸው ጥበቃና ዋስትና የሚሰጥ መሆን እንዳለበት በአቋም መግለጫቸው ያሰፈሩት የቪዥን ኢትዮጵያ ተወያዮች፤የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶችን፣ የነጋዴ ማህበራትን፣ተማሪዎችን፣ወጣቶችን፣ የሴቶች ድርጅቶችን የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ  በሰላም ግንባታ ሂደቱ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው አስምረውበታል።

ከካውንስሉ ተግባራት አንዱ ትክክለኛ የእውነት አፈላላጊና የእርቅ ኮሚሽን የሚቋቋምበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ይህ ኮሚሽንም ከፖለቲካ አመለካከት ጋር በተያያዘ አላግባብና ከህግ ውጪ በተፈጸሙ ግድያዎች፣ ማሰቃዮቶችና ድብደባዎች ዙሪያ ምርመራ ያደርጋል።

እንዲሁም ነጻ፣ገለልተኛ፣ ተዓማኒና ውጤታማ የሆነ የምርጫ ቦርድ ማቋቋም የካውንስሉ ተግባር እንደሚሆን የገለጹት የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች፤ የምርጫውንም ሂደት በሰላማዊ መንገድ እውን ለማድረግ ብቃት ያላቸው፣ ገለልተኛ የሆኑና በሁሉም የሀገሪቱ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሚኖራቸው የምርጫ አስፈጻሚዎች መሰየም  እንደሚኖርበት በመግለጫቸው አስፍረዋል። ሌሎችንም ከነዚህ ነጥቦች ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አቋሞች በመግለጫቸው ያንጸባረቁት የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች፤

አሁን ሀገሪቱን እየገዛ ያለው ቡድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በቶሎ እንዲያነሳ፣ ግድያና በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የሚፈጽመውን እስር እንዲያቆምና  የህዝቡን የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች እንዲያከብር ጠይቀዋል። በተመድ የሰባአዊ መብት ካውንስል ቡድን፣ ሀገራዊ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ሌሎች ታማኝ ዓለማቀፍ ድርጅቶች  በሀገሪቱ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ  የደረሰውን ጉዳት በገለልተኝነት ምርመራ  እንዲያደርጉ ይፈቅድ ዘንድም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።

በስውር የማጎሪያ እስር ቤቶች የሚሰቃዩትን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ  የጠየቁት የቪዥን ኢትዮጵያ ተሰብሳቢዎች፤ በአዲስ አበባ ባሉ ዲፕሎማቶች ላይ የተጣለው የመንቀሳቀስ ገደብም እንዲነሳ አሣስበዋል።