ኢሳት (ጥቅምት 15 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ሃገሪቱን የሚጎበኙ የውጭ ሃገር ቱሪስቶች ቁጥር በመቀነስ ላይ መሆኑ ተገልጸ።
መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት ዲፕሎማቶች ከመዲናይቱ 40 ኪሎሜርት ርቀው እንዳይሄዱ የተቀመጠው እገዳ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ ሃገር ዜጎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ታውቋል።
መንግስት ዲፕሎማቶቹ ከመዲናይቱ 40 ኪሎሜርት ርቀው ሲሄዱ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ያለባቸው ለደህንነታቸው ነው ሲል መግለጹ ይታወሳል።
ይሁንና፣ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የውጭ ሃገር ጎብኚዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር እና ለመጎብኘት ማንንም አካል ማሳወቅ አይጠበቅባቸውም ሲል ሰኞ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት በበኩሉ ጉብኝታቸውን የሚሰርዙ ቱሪስቶች መኖራቸውን አረጋግጦ ቁጥሩ ግን እየቀነሰ መጥቷል ሲል ምላሽን ሰጥቷል።
በአስጎብኚነት ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችና ሆቴሎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ የቱሪስቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ይገልጻሉ።
መንግስት ሃገሪቱ በቀጣዮቹ አምስት አመታት ከአምስት የአፍሪካ የቱሪስት ማዳረሻዎች መካከል አንዷን ለማድረግ እቅድ መደፉ ታውቋል።
ይሁንና በተለይ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ህዝባዊ ተቃውሞና አለመረጋጋት ሃገሪቱን በሚጎበኙ የውጭ ቱሪስቶች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
በተያዘው አመት የኢትዮጵያ የቱሪስት መስህቦችን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የውጭ ሃገር ቱሪስቶች ይጎበኛሉ ተብሎ ቢጠበቅም ቁጥሩ ሊቀንስ እንደሚችል ተገምቷል።