ጥቅምት ፲፩ (አሥራ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመላው አገሪቱ የሚታየውን የለውጥ ፍላጎት ተከትሎ የህልውና ጥያቄ የተነሳበት ህወሃት /ኢህአዴግ በተለያዩ ከተሞች ህዝቡ ዲሹን እንዲያወርድ፣ ካላወረደ ግን እርምጃ እንደሚወሰድበት ማስታወቂያ እያስነገረና በተግባርም በካድሬዎቹ አማካኝነት ዲሾችን እያስወረደ ነው።
በአርባ ምንጭ ከተማ ህዝቡ በሚቀጥሉት 3 ቀናት ዲሹን ካላወረደ እርምጃ እንደሚወሰድበት ካድሬዎች እየዞሩ በመቀስቀስ ላይ ሲሆን፣ አንዳንድ ሰዎች ዲሾቻቸውን ማውረድ ቢጀምሩም ፣ የሚመጣውን ለመቀበል ዝግጁ የሆኑ ሰዎች መኖራቸውም ታውቋል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ በለገጣፎና አካባቢዋ ዲሽ ለማስወረድ የሚደረገው ጥረት በህዝቡ እምቢተኝነት እስካሁን አልተሳካም። በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ዲሾቻቸውን ያወረዱ ሰዎች ቢኖርም፣ አብዛኛው ህዝብ አላወረደም። በጎንደር እና በባህርዳር ዲሽ የማስወረዱ እንቅስቃሴ እስካሁን የታሰበውን ያክል ውጤት አላመጣም።
ወጣቱ ከውጭ እና ከአገር ውስጥ የሚሰራጩ መረጃዎችን በፌስቡክ እና በሌሎችም የመገናኛ ዘዴዎች እንዳይከታተል የሞባል ኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦበታል። አንዳንድ ወጣቶች የኢንተርኔት አገልግሎት ወደሚሰጡ ሆቴሎች በመሄድ ለመጠቀም ቢሞክሩም፣ እርሱም ለወደፊቱ አስተማማኝ እንደማይሆን እየገለጹ ነው።
በአዲስ አበባ የሚኖሩ አንዳንድ ወጣቶች አፈናው በእጅጉ እንዳስመረራቸውና ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ እንደተጋቡ ተናግወረዋል ። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የግለሰቦችን የግል መሳሪያ ለመቀማት የሚደረገው ሙከራ በአብዛኛው ያልተሳካ ሲሆን፣በአንዳንድ አካባቢዎች መሳሪያ ለመንጠቅ የሄዱ ሰዎች ከገበሬዎች ተኩስ ተከፍቶባቸዋል።
ትናንት ሌሊት በምዕራብ ጎጃም ዞን በጢስ አባይ ከተማ በሃይል ማመንጫው ግቢ የሰፈሩ የመከላከያ ሰራዊት ከአካባቢው ታጣቂዎች ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል። በታጣቁ የአካባቢው ነዋሪዎች እና በመከላከያ አባላቱ በነበረው የተኩስ ልውጥጥ ምን ያክል ሰዎች እንደተጎዱ የታወቀ ነገር የለም።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ኦክላንድ ኢንስቲቲዩት ባወጣው መግለጫ ዋናው የተቃውሞው መነሻ ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለዲሞክራሲ ፣ ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽና በነጻነት ለመሰብሰብ ቢሆንም፣ አሁን የተወሰደው እርምጃ ግን ይህን የሚደፈጥጥ ነው ብሎአል። ኢትዮጵያ ህጋዊ ባልሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለረጅም ጊዜ ስትገዛ የቆየች አገር መሆኗ ይታወቃል የሚለው ኦክላንድ ኢንስቲቲዩት፣ አሁን የሚወሰዱት የአፈና እርምጃዎች የአገሪቱን ችግሮች አይፈቱም ብሎአል።አገዛዙ ለአመታት ሲያራምድ የነበረውን ጭቆና ለመግፋት መወሰኑን የሚያሳይ ነው ሲል አክሏል። የአለማቀፉ ማህበረሰብ አዋጁን እንዲያወግዝም ጠይቋል። ይህን የማያደርጉ ከሆን ግን ለጋሽ አገራት አሜሪካ ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩት ሲገደሉና በሺዎች የሚቆጠሩት ሰታሰሩ አብረው እንደተባበሩ ይቆጠራል ብሎአል።