ጥቅምት ፲፩ (አሥራ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ በአንዳንድ ከተሞች የትግራይ ተወላጆች መፈናቀላቸውን የሚያሳይ ዘገባ በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ከቀረበ በሁዋላ አሁንም ክልሉን እየለቀቁ የሚሄዱ ሰዎች መኖራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።
በላሊበላ ሆስፒታል ሲሰሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ወደ ትግራይ የሄዱ ሲሆን፣ ለምን አካባቢውን ለቀው መሄድ እንደፈለጉ ሲጠየቁ ምንም መልስ አለመስጠታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
“ከአማራ ክልል ለተፈናቀሉ መሬትና ገንዘብ ይሰጣል” የሚል ቅስቀሳ ተጠናክሮ መቀጠሉ ምናልባትም ሰዎች አካባቢውን እየለቀቁ እንዲሄዱ ሳያደርጋቸው እንደማይቀር ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በመተማ በነበረው ተቃውሞ በከተማ ይኖሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደ ውጭ አገር እንደትሄዱ ሁኔታዎችን አመቻችቶላችሁዋል የሚል ቅስቀሳ በህወሃት ካድሬዎች ከተነገራቸው በሁዋላ ብዙዎች ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን ጉዳዩን በቅርበት የሚከተታሉ ሰዎች ለኢሳት ተናግረዋል።
አሁንም ለተፈናቃዮች የተለዬ ነገር እንደሚደረግ የሚደረገው ቅስቀሳ ህወሃት በህዝቦች መካከል ቅራኔ ለምፈጠር የሚጠቀምበት ስልት በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እነዚህ ወገኖች ምክራቸውን ለግሰዋል።