ኢሳት (ጥቅምት 10 ፥ 2008)
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ የተስፋ መቁረጥ ሁኔታ እንደሆነ የቀድሞ የአየር ሃይል አባላት ገለጹ።
የቀድሞ አየር ወለድ 2041ኛ ብርጌድ የነበሩት ሻለቃ ሱራፌል ዘውዴና፣ የቀድሞ አየር ሃይል አብራሪና የበረራ መምህር የነበሩት ካፕቴን ተሾመ ተንኮሉ ለኢሳት እንደተናገሩት፣ ህዝብ ነጻነቱን ወደ እጁ ለማስገባት እየተዘጋጀ ባለበት ጊዜ ህወሃት እንደማንኛውም አምባገነን ስርዓት እየተፍጨረጨረ እንደሆነ አስረድተዋል።
ህወሃት/ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ህዝብ በፊትም የሰጠው የዴሞክራሲ መብት የለም አሁንም የከለከለው ነጻነት የለም ያሉት የቀድሞ የጦር ሰራዊት አባላት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተንተርሶ አገዛዙ እያደረገ ያለው የመብት ጥሰት ቀድሞ ሲያደርግ ከነበረው የተለየ አለመሆኑን ተናግረዋል። በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ለህዝባዊ ተቃውሞ የወጣው ህዝብ የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በፈቀደለት ነጻነት ሳይሆን በገዘ ፈቃዱ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ሻለቃ ሱራፌል ዘውዴ፣ አዋጁ አስጊ በሆኑ ወታደራዊ ቀጠናዎች የሚወጣ አዋጅ እንጂ፣ አሁን ወያኔ እንዳደረገው በመላ አገሪቷ የሚታወጅ እንዳልነበር ገልጸው፣ አዋጁ መላዋን አገሪቷን የጦር ቀጠና አድርጓታል ብለዋል። በመሆኑም፣ ለአገዛዙ አዲስ አበባን ጨምሮ አስጊ ያልሆነ ቦታ እንደሌለ አመላካች እንደሆነ የሚያስረዳ ነው ሲሉ ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ተናገረዋል።
የህወሃት የመከላከያ መሪዎች፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው በአንድ በኩል ለህዝብ ጥቅም ነው እያሉ፣ በሌላ በኩል ህዝብን ጨፍልቆ የመግዛት እርምጃ መውሰዳቸውን የተናገሩት ሻለቃ ሱራፌል ዘውዴ አላማቸውም የኢትዮጵያ ህዝብን አስፈራርቶ ለመግዛት እንዳሰቡ አመላካች ነው ሲሉ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነቱ አስፋላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ስርዓቱ ከህዝቡ ጋር የተለያየበት ሁኔታ ተፈጥሯል ያሉት ካፕቴን ተሾመ ተንኮሉ፣ አሁን ያለው ሁኔታ ነጻ የትግል መሬት ለመፍጠር አመቺ እንደሆነ ተናገረዋል። የህወሃት መሪዎች ህዝብ እያሸነፈ መምጣቱን በመረዳታቸው አጥፍቶ ለመጥፋት እየተዘጋጁ እንደሆነ እኚሁ የአየር ሃይል ባለሙ ተናገረዋል።
ህዝብ ምን ማድረግ አለበት ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ፣ በኢህአዴግ አባልነት የተመዘገቡ የከፍተኛና የበታች ካድሬዎች ህዝብ ጋር በመሆን ህወሃትን መታገል አለባቸው ሲሉ ሻለቃ ሱራፌል ዘውዴ ጥሪ አቅርብገዋል። ካፕቴን ተሾመ ተንኮሉ በበኩላቸው ለህወሃት መሪዎች ነጻ የሆነ መሬት የለም፣ ከህዝቡ ጋር ደም ተቃብተዋል ሲሉ ገልጸው፣ ያላቸው ምርጫ ስልጣን መልቀቅ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።