ኢሳት (ጥቅምት 9 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ ከ800 በላይ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ህዝባዊ ተቃውሞ ዕልባት ከመስጠት ይልቅ ሊያባብሰው እንደሚችል አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።
መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አዋጁ መሰረታዊ የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶችን አደጋ ውስጥ ከትቶ እንደሚገኝ ስጋቱን ገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል ለወራት ዘልቆ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ከ800 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን ያስታወሰው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ተጨማሪ የሃይል ዕርምጃዎችን ተግባራዊ ማደረጉ ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል ሲል በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ የልማት አጋር የሆኑ ሃገራትን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ታዋቂ ግለሰቦች ለስድስት ወር ይቆያል የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት አስተዋጽዖ እንደሚኖረው በመግለጽ ላይ ናቸው።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአህጉራዊ ንዑስ ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት ሙቶኒ ዋንየኪ ከህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገኛኘ ለእስር የተዳረጉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ጦማሪያን በአስቸኳይ መፈታት እንዳለባቸው ከብሉምበርግ የዜና አውታር ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታውቀዋል።
በሃገሪቱ ያለው የፖለቲካ ውጥረት መሻሻልን ከማሳየት ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱንና የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ትኩረት መሆኑን ሃላፊው አክለው ተናግረዋል።
በአስቸኳይ አዋጁ ዙሪያ ሪፖርትን ያቀረበው ብሉምበርግ የዜና አውታር በበኩሉ የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ዘግቧል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ተግባራዊ የተደረግው ይኸው አዋጅ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ያለ-ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተጠርጣሪ የተባሉ ሰዎችን እንዲያሰሩና አስፈላጊውን ዕርምጃ እንዲወስዱ ፈቃድን ይሰጣል።
ይሁንና አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች አካላት አዋጁ ችግሮችን ከማባባስ ይልቅ የሚያመጣው መፍትሄ አይኖርም በማለት ቅሬታን እያቀረቡ ይገኛል።
አጨቃጫቂ ነው የተባለው የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ መደረግ ተከትሎ በተለይ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የጅምላ እስር እየተካሄደ መሆኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።