በጎንደር የሥራ ማቆም አድማው ለሶስተኛ ቀን ቀጥሎአል

ጥቅምት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከፍተኛ ማስፈራሪያ፣ እስርና እንግልት የደረሰባቸው በርካታ የጎንደር ከተማ ነጋዴዎች  የመጨረሻውን ቀን የሥራ ማቆም አድማ ተግባራዊ አድርገዋል። የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸው አራዳና ሁለገብ የገበያ ማእከል እንደተዘጉ ውለዋል። በርካታ ነጋዴዎች ድማውን ተከትሎ ታስረዋል።

ጎንደር እና ባህርዳር  የሥራ ማቆም አድማውን በማድረግ አዋጁን ወድቅ ያደረጉ የመጀመሪያዎቹ ከተሞች ሆነዋል። በባህርዳር ተደርጎ ከነበረው የሥራ ማቆም አድማ በሁዋላ አገዛዙ የበቀል እርምጃውን በማሳረፍ ላይ መሆኑን የክልሉ ወኪላችን የላከችው ሪፖርት ያመለክታል።

በመጀመሪያው የአድማ ቀን ጥቅምት 1/2009 ዓም. አብዛኛው የከተማዋ የንግድ ማዕከላት ዝግ ሆነው ማርፈዳቸውን ያስታውሰችው ዘጋቢያችን፣ ከአሁን በፊት በነበሩት አድማዋች “የንግድ ሱቃችሁን ዘግታችኋል፣ነጋዴው ህብረተሰብ በመንግስት ላይ እንዲያድም ገፋፍታችኋል እና መንግስት የሚያወጣውን የእገዳ መመሪያዎች ጥሳችኋል” በሚል ሰበብ ለ24 ሰዓት ያሰሩዋቸውን ነጋዴዎች በመደወልና በየቤታቸው በመሄድ የተገኙትን ራሳቸውን ያልተገኙትን ቤተሰቦቻቸውን አስፈራርተው አንዲከፍቱ አደርገዋል፡፡

በሁለተኛው የስራ ማቆም አድማ ቀን  ደግሞ  ለግማሽ ቀን እንዲከፍቱ ተገደው የነበሩ ነጋዴዎች ግዳጁን በመጣስ ሱቃቸውን ዘግተዋል፡፡በዚህ የተበሳጩት  ካድሬዎች ከሃያ የሚበልጡ ነጋዴዎችን አሰርዋል፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ አሁንም በእምቢተኝነቱ በመቀጠል አድማውን ለሶስተኛ ቀን  ከቀጠሉ በሁዋላ ነጋዴዎች እንደታሰሩ መረጃ ያገኘው አብዛኛው ነጋዴ ስልኩን በመዝጋት ከአገዛዙ ጋር የተጋባውን እልክ አስጨራሽ ትግል በአሸናፊነት ተወጥቶታል፡፡የህውሃት /ኢህአዴግ ወኪሎች  ቀንና ሌሊት በመሯሯጥ  በዕለቱ ያገኟቸውን ነጋዴዎች ሲያስሱና ሲያስሩ አደርዋል፡፡

በአራተኛው  ቀን ጠዋት  ላይ  አድማው በተመሳሳይ ሁኔታ መቀጠሉን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ የተበሳጩት ካድሬዎች ለታሰሩ ነጋዴ ቤተሰቦች ስልክ በመወደወል ሱቆችን ካልከፈቱ ወደ አልታወቀ ቦታ ነጋዴዎችን በመውሰድ ስቃይ እንደሚደርስባቸው በመዛት የተወሰኑ ሱቆች እንዲከፈቱ አድርገዋል፡፡ሆኖም የሶስቱም ገበያ ውስጥ  ሱቆች፣የኮስሞቲክ ሱቆችና ሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆችን ማስከፈት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡አራተኛው ቀን በከፊል በተከፈቱና በከፊል በተዘጉ የንግድ ቤቶች የዋለችው ባህር ዳር፣  የከፈቱትም ተገደው በመክፈታቸው ሽያጭ ለማካሄድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በራቸውን በከፊል ከፍተው ውለዋል፡፡

በአምስተኛው ቀን አራቱን ቀን በትግል ያሳለፉት የባህር ዳር ገበያ ውስጥ ነጋዴዎችን ከያሉበት በማሰባሰብ እንዲከፍቱ አስገድደዋል።በእምቢታቸው የጸኑትን ነጋዴዎችም አስረዋል፡፡

ባህር ዳር በዚህ አይነት የስራ ማቆም አድማዋን ስታጠናቅቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ  ታጣቂዎችና ካድሬዎች አልፎ አልፎ በየሰፈሩ በመግባት ሁለተኛ ሪሲቨር ያላቸውን ዲሾች በማውረድ ሲያሻቸው በመሰባበር የሚግባቡዋቸውን ሰዎች ኤልኤንቢ አውርደው በመስጠት ሰፈሮችን ማመሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ይህ ድርጊት በገዥው መንግስትና በህብረተሰቡ መካከል ያለውን ክፍተት የበለጠ በመጨመር ወደ ምሬት እየወሰደው ነው፡፡ህብረተሰቡ ዛሬ ዲሾችን ቢያወርዱበትም መልሶ በማስተካከል  ስርጭቶችን መከታተሉን  ግን አላቋረጠም፡፡

እርምጃው ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ሲሆንበት አገዛዙ  በዲሽ ስራ የሚተዳደሩ ወጣቶችን እየያዙ በማሰር ላይ ናቸው፡፡ወጣት ባለሙያዎች የሚታሰሩት በአካባቢው ባሉ የቀበሌ አመራርና ለስርዓቱ ባደሩ አባሎች ሲሆን በስራ አጋጣሚ ፣በቤተሰብና በግል ጉዳይ ችግር የነበረባቸውን ባለሙያዎች ያለምንም ማስረጃ  ” ኢሳትን ትገጥማላችሁ ” በሚል ሰበብ ወደ ወህኒ በመውሰድ ላይ ናቸው፡፡በከተማዋ የሚገኙትን የዲሽ ባለሙያዎች ስልክ በመደወል ” ኢሳትን ትገጥማላችሁ? “በማለት መጠየቅና ማሰር እየተለመደ መምጣቱን የክልሉ ዘጋቢአችን ገልጻለች።

በሌላ በኩል በአርማጭሆ ወረዳ ሙሴ ባምብ ማሪያም መዘጋ ላይ አንድ ወጣት በአጋዚ ወታደሮች ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ታውቋል። እባበይ ፈለቀ የተባው ወጣት ጠመንጃውን ይዞ በሞተር ሳይክል ሲጓዝ ወታደሮች ድንገት አስቁመው መሳሪያውን እንዲያወርድ ሲጠይቁት ፣ ፈጣን እርምጃ ወስዶ ማምለጡ ታውቋል።

አርሶአደሮች ትጥቃቸውን እንደማይፈቱ በተደጋጋሚ እያስታወቁ ሲሆን፣ ትጥቅ የማስፈታቱ እንቅስቃሴ ከቀጠለ ብዙ ደም መፋሰስ ሊከሰት እንደሚችል ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ።