በሰላማዊ ትግል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅት አባላት ኢላማ ሆነዋል

ጥቅምት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ምንጮች እንደገለጹት የኦፌኮና የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እየታደኑ በመታሰር ላይ ሲሆኑ፣ ብዙዎችም ሸሽተዋል። ናዚ ያላደረገውን ስራ እየተሰራ ነው የሚሉት እነዚህ የተቃዋሚ አባላት፣ ማንም የሁለቱ ፓርቲዎች አባላት ተቃወሙም አልተቃወሙም እየተያዙ መሆናቸውን ገልጸዋል። አብዛኛው እስር የሚፈጸመው በኦሮምያ ክልል ሲሆን፣ የተቃዋሚ ድርጅት አባላቱ የቻሉት ጫካ ያልቻሉት ደግሞ አካባቢውን ለቀዋል።

በርካታ ወጣቶች እየተደደቡ ሲሆን፣ ሁለት ወጣቶችም በጥይት መገደላቸውን የፖለቲካ ድርጅት አባላት ገልጸዋል። በሌላ በኩል በኢትዮጰያ የተደነገገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውጥረቱንና ያለመረጋጋቱን እያባባሰው እንደሆነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልጿል።

ካለፈው ዓመት ማገባደጃ ጀምሮ የኢትዮጰያ መንግስት  በኦሮሚያና  አማራ ክልሎች የተቀሰቀሱበትን ተቃውሞዎች ለማቆም  በወሰደው የሃይል እርምጃ  ከ800 በላይ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል ብሎአል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ፣ የአፍሪካ ቀንድና የታላላቅ ሃይቆች አካባቢ ዳይሬክተር  ሙቶኒ ዋኔኪ ” አሁን በመንግስት  የተደነገገው  አዋጅ  በጣም ከባድ ቅጣቶችን የያዘና  በአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት እንኳ  ሊደፈሩ የማይገባቸውን  መሰረታዊ የሆኑ ሰብአዊ መብቶችን አደጋ ላይ የጣለ  ነው” ብለዋል።

አክለውም፦” ይህ  ስጋትና አደጋ   በትክክል በባለስልጣናቱ ሊታውቅ ይገባል። ወደፊት የሚደረገው የሃይል እርምጃና የሰብአዊ መብት ጥሰት ሁኔታውን ያከፋዋል እንጅ አያበርደውም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በሌላ በኩል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት  ሳማንታ ፓዎል የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነችው ብሌን መስፍን ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንድትፈታ ጠይቀዋል።

ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ሰላማዊ ፖለቲከኞችን እንዲለቀቁም አሳስበዋል። አምባሳደሩ በአገሪቱ የቀጠለው አፈናና ጥቃት እንዲቆም ገዢውን ፓርቲ በድጋሜ ጠይቀዋል።