ከእስር ቤት ለምስክርነት የተጠሩት  ሦስቱም ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት  ሳይቀርቡ ቀሩ

ጥቅምት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት በጋዜጠኛ ኤልያስ  ገብሩ  እና  አምሳሉ ገ/ኪዳን  የነበረው  ምስክር የመስማት ቀጠሮ  መስካሪዎቹ በ እስር የሚገኙት ሶስቱም ጋዜጠኞች  ሳይገኙ ቀርተዋል።

ለምስክርነት  ተቀጥረው የነበሩት  እስረኞች  ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝንና ውብሸት ታዬ ናቸው። የቃሊቲ ማረሚያ ቤት  እስክንድርን ያላቀረበበትን ምክንያት በገለጸበት ደብዳቤ”እስክንድር ነጋ በማረሚያ ቤት ታራሚዎችን ለረብሻ እና ብጥብጥ እያነሳሳ ይገኛል። …ለፖሊስ የእጀባ ሥራም አደጋ ይፈጥራል። በዚህ የተቸገርን መሆኑን ፍርድ ቤቱ ይረዳልን”ብሏል።

ማረሚያ ቤቱ እንዲህ ብሎ የዋሸው እስክንድርና ሌሎች አራት ሰዎች ለብቻቸው ታስረው በሚገኙበት ሁኔታ መሆኑ፤ ባለቤቱን ሰርካለም ፋሲልንና በርካታ ወዳጆቹን አስቆጥቷል። የዝዋይ ማረሚያ ቤት  ደግሞ  ተመስገን ደሳለኝን እና ውብሸት ታየን አላቀረበው  የትራንስፖርት ችግር ስላጋጠመው እንደሆነ በደብዳቤ አሳውቋል።

“ታራሚዎችን የሚያመላልሰው መኪና ተበላሽቶ ለጥገና አዲስ አበባ መጥቶ ስላልተመልሰ ተመስገን ደሳለኝንና ውብሸት ታዬን በቀጣይ ቀጠሮ እንድናቀርብ ከይቅርታ ጋር እንጠይቃለን” -በሏል የዝዋይ ማረሚያ ቤት በደብዳቤው።

በዚህም  የተነሳ ምስክሮችን ማድመጥ ሳይቻል በመቅረቱ  ዳኛው ለታህሳስ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። የቃሊቲ ማረሚያ ቤት በቂ ምክንያት ባለማቅረቡም እስክንድር ነጋን በተከታዩ ቀጠሮ በቂ አጃቢ ተመድቦለት እንዲቀርብ ዳኛው አዘዋል።