የተመድ ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብር አሳሰቡ

ኢሳት (ጥቅምት 8 ፥ 2009)

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባን ኪ ሙን የኢትዮጵያ መንግስት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብር አሳሰቡ።

ሃገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ማድረጓን ያወሱት ዋና ጸሃፊው አዋጁን ምክንያት በማድረግ የሰብዓዊ መብቶች ሊጣሱ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ገልጸዋል። የአስቸኳይ አዋጁን ተግባራዊ መደረግን ተከትሎ አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ቃል አቀባይ የሆኑት ስቴፋኒ ጁጃሪክ የአዋጁን መውጣትን ተከትሎ ባን ኪ ሙን የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ በስጋት እየተከታተሉት መሆኑንም ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ዋና ጸሃፊው በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ችግር ዕልባት ለመስጠት ሁሉንም አሳታፊ የሆነ ድርድር መካሄድ እንደሚገባውና የሃይል ዕርምጃ እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸውንም አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት ይሆናል በሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛል።

የአሜሪካ መንግስት በአዋጁ መውጣት ያደረበትን ስጋት ለሁለተኛ ጊዜ ይፋ በማድረግ በሃገሪቱ መሰረታዊ የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪውን ማቅረቡ ይታወሳል።

የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ህጉን በመኮነን መግለጫ ማውጣታቸው መዘገቡ ይታወቃል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መደረግን ተከትሎ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች የጅምላ ዕስራት በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።