ኢሳት (ጥቅምት 8 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ መንግስት ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ከቀናት በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አስመልክቶ በርዕሰ-አንቀጹ ባሰፈረው ፁሁፍ ቅሬታውን አቀረበ።
አለም አቀፍ ተነባቢነት ያለው ጋዜጣው ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው አዋጅ የአምባገነን መሪዎች የሚጠቀሙበት ስልት እንደሆነ በመግለጽ አዋጁ ሊሰራ የማይችል ነው ሲል አቋሙን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ይሁንና፣ የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ በአሜሪካ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ በጻፈው ጹሁፍ ቅሬታውን እንዳቀረበ ጋዜጣው አመልክቷል።
በኤምባሲው ኮንሱላር ሚኒስትር የሆኑት አቶ ተስፋዬ ወልዴ ጋዜጣው አዋጁን የማይሰራ ነው ሲል የገለጸውን አቋም በመንቀፍ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውጤታማ ይሆናል ሲሉ ለጋዜጣው ባቀረቡት የቅሬታ ጹሁፍ ገልጸዋል።
የአስቸኳይ አዋጁን ተግባራዊ መደረግን ተከትሎ አለም አቅፍ ተነባቢ የሆነው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ አዋጁ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሊያስፋፋ እንደሚችልና ድርጊቱም የአምባገነን መንግስታት መግለጫ እንደሆነ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።
በአዋጁ ዙሪያ አቋሙን ይፋ ያደረገው ጋዜጣው የአውሮፓ የህብረትና የአሜሪካ መንግስት ከሃገሪቱ ጋር ያላቸውን ጥቅም ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚኖርባቸውም ጠይቋል።
በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለቀን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ጋዜጣው ተመሳሳይ አቋምን ይዞ የነበረ ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግስትም ለሰብአዊ መብት ከመክበር ቅድሚያን እንዲሰጥ አሳስቦ እንደነበር ይታወቃል።
ሃገሪቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጸረ-ሽብር ዘመቻ ትብብር ቢኖራትም ወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ልዩ ትኩረትን የሚሻ ነው ሲል ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ይገልጻል።
ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ እየወሰደ ነው ባለው የሃይል ዕርምጃ ከ500 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ጋዜጣው የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ በዘገባው አስፍሯል።
የተባበሩት መንስታት ድርጅትን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ እንዲሁም የተለያዩ አካላት ግድያው በገለልተኛ አካላት ማጣራት እንዲካሄድበት በመጠየቅ ላይ ናቸው።
መንግስት በበኩሉ ማጣራቱ በሃገር በቀል ድርጅቶች ላይካሄዳል በማለት ጥሪውን ሳይቀበል ቀርቷል።