ኢሳት (ጥቅምት 7 ፥ 2009)
በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ ተካሄዶ ከነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ወደ 1ሺ አካባቢ ተጠርጣሪዎች በንብረት ላይ ውድመትን አድርሳችኋል ተብለው በቁጥጥር ስር ዋሉ።
የከተማዋ አስተዳደር በቁጥጥር ስር የዋሉትን አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች ከሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች የመጡ እንደሆነና ከ50 የማይበልጡት ብቻ የሰበታ ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጿል።
የአስቸኳ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መደረገን ተከትሎ በአንድ ከተማ ብቻ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ሰው ሲታሰር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በተለያዩ የኦሮሚያና ሌሎች የክልል ከተሞች ተመሳሳይ እርምጃዎች እየተወሰድ መሆኑንም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ለእስር የተዳረጉ 1ሺ አካባቢ ሰዎች ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን የተናገሩት የሰበታ ከተማ ከንቲባ አቶ ኣራርሳ መርዲሳ ምርመራው እንደተጠናቀቀ ንብረት አውድመዋል በተባሉት ላይ ክስ እንደሚመሰረት አስታውቀዋል።
የከተማዋ አስተዳደር በከተማዋ ተካሄዶ ከነበረ ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ 11 ፋብሪካዎች ወድመዋል ሲል ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ከእሬቻ በዓል አከባባር ጋር በተያያዘ በቢሾፍቱ ከተማ የደረሰውን ዕልቂት ተከትሎ የሰበታ ከተማን ጨምሮ በበርካታ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ መሰንበቱ የሚታወቅ ነው።
ከዚሁ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በርካታ ነዋሪዎች መታሰራቸው ይነገራል። የገቡብት ያልታወቁ ሰዎች መኖራቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ይገልጻል።
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከኦሮሚየ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን 17 ሰዎች በሽብርተኛ ክስ ከሷል። ተጨማሪ ሰዎች በተመሳሳይ ክስ ለእስር እየተዳረጉ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።