ኢሳት (ጥቅምት 7 ፥ 2009)
ባለፈው ሳምንት ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ መንግስት በማህበራዊ ድረገጾች ላይ ከፍተኛ ነው የተባለ ቁጥጥር መዘርጋቱን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሰኞ ዘገቡ።
የሃገሪቱ ዜጎች ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በድረገ-ጾች ላይ ምንም አይነት ጽሁፉ እንዳያሰፍሩ እገዳ እንደተጣለባቸውና ድርጊቱ ተጨማሪ ውጥረት ማንገሱን አፍሪካ ነውስ ኤጀንሲ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ዘገባ አመልክቷል።
በአዋጁ ተግባራዊነት ዙሪያ ዝርዝር መረጃን የሰጡ የመንግስት ባለስልጣናት በዚሁ አዋጅ መሰረት መቀመጫቸውን ከአዲስ አበባ ያደረጉ የውጭ ሃገራት ተወካዮች ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ሳያሳውቁ ከመዲናይቱ 40 ኪሎሜርት ርቀው እንዳይጓዙ እገዳ ተጥሎባቸዋል።
እርምጃው ለአምባሳደሩ ደህንነት ነው ቢባልም የየሃገራት ተወካዮች ባለፈው ሳምንት በኢንተርኔት አጠቃቀም ላይ የተጣለውን እገዳ እንዲነሳና መንግስት ተጨማሪ ማብራሪያን እንዲሰጣቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ለእነዚህ አለም ቀፍ ተቋማት ስጋትን አሳድሮ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማንኛውም ሰላማዊ ሰልፍ እንዲሁም ህዝባዊ ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ እገዳን ጥሏል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችን የማሰር፣ የመመርመር፣ እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶችን የመፈተሽ ስልጣን የተሰጣቸው ሲሆን በትምህርት ተቋማት ዙሪያ ቁጥጥር እንዲካሄድ በአዋጁ ሰፍሯል።
የብሪታኒያው የማሳረጫ ጣቢያ (BBC) በበኩሉ የአዋጁ ተግባራዊነትን ተከትሎ የጅምላ እስራት እየተካሄደ መሆኑን ሰኞ ዘግቧል።
ሌሎች በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁ አዋጁ በሃገሪቱ ዜጎች ላይ ካሳደረው ስጋት በተጨማሪ በአለም አቀፍ ተቋማትና የሃገራት ተወካዮች ዘንድም መነጋገሪያ ሆኖ መቀጠሉን በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረቡት ሪፖርት አመልክተዋል።