ኢሳት (ጥቅምት 3 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ እየተባባሰ መጥቷል ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ግምት ውስጥ በማስገባት የአውሮፓ ህብረትና የአለም አቀፍ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወስዱ ተጠየቀ።
የአውሮፓ ፓርላማ ንዑስ ኮሚቴ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ባዘጋጀው መደረክ ላይ የታደመው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እጅጉን አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አብራርቷል።
በመድረኩ ለተሳተፉ የአውሮፓ ህብረትና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተወካዮች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ኣፋጣኝና ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወስዱ አሳስቧል።
ህብረቱም ሆነ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ከሃገሪቱ ጋር ያላቸውን የጥቅም ትስስር በማስቀደም በቂ ትኩረት እየሰጡ እንዳልሆነና ድርጊቱ ተገቢ አለመሆኑን የሂህማን ራይትስ ዎች ተወካዮች በመድረኩ ቅሬታቸውን አስተጋብተዋል።
የኢትዮጵያ የልማት አጋር የሆነ የአውሮፓ ህብረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የተፈጸሙ ግድያዎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያጣራ ግፊትን ማድረግ እንዳለበት በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆርን ለመገኛና ብዙሃን አስታውቀዋል።
በመድረኩ ታዳሚ የነበሩ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት የጀርመኗ ቻንስለር አንጀላ መርከል በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት በመኮነን ተቃውሞ ማሰማታቸውንም ለመረዳት ተችሏል።
መርከል ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጥሪን ቢያቀርቡም ጀርመን በአውሮፕላ ህብረት ካላት አስተዋፅዖ እና ሃላፊነት አንጻር ሲነጻጸር ቀርቦ የነበረው ጥሪ ደካማ እንደነበር የፓርላማ አባል አና ጎሜዝ ለVOA እንግሊዝኛው ክፍል አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ፓርላማ ቀርበው ንግግርን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልነበሩት አንጀላ መርከል የኢትዮጵያ መንግስት እየቀረቡ ላሉ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የአውሮፓ ህብረት በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተፈጽሟል ያላቸውን ግድያዎች በማውገዝ ድርጊቱ በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበርት ሲያሳስብ ቆይቷል።
አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራትና ተቋማት ተመሳሳይ ጥሪን ቢያቀርቡም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተባባሪ እንደማይሆኑ ምላሽ ሰጥተዋል።