በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከ500 ሰዎች በላይ መሞታቸውን የኢትዮጵያ መንግስት አመነ

ኢሳት (ጥቅምት 3 ፥ 2008)

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሲካሄዱ ከነበሩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ጋር በተገናኘ ከ500 በላይ ሰዎች መሞታቸውን መንግስት አመነ።

ሂውማን ራይትስ ዎችና ሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ለወራት በዘለቀው በዚሁ ተቃውሞ ከ700 የሚበልጡ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ሲገልፅ ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በኦሮሚያ ክልል ብቻ 170 ሰዎች፣ በአማራ ክልል ደግሞ 120 አካባቢ ሰዎች መሞታቸውን በመግለፅ በአጠቃላይ ከተቃውሞ ጋር በተገናኘ ከ500 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ለጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።

ድርጊቱ በአለም አቀፍ ገለልተኘ አካል ምርመራ እንዲካሄድበት ጥያቄን እያቀረቡ ያሉ አካላት ትክክለኛ የሟቾች ቁጥር ሊታወቅ የሚችለው ምርመራው ሲካሄድ ብቻ መሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው።

ይሁንና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የቀረበን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የጸጥታ ሃይሎች የፈጸሙት ድርጊት በሃገር በቀል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በኩል እንደሚከናወን ሲገልፁ ቆይተዋል።

ይካሄዳል የተባለው ይኸው የምርመራ ሂደት ግን በማን እና መቼ እንደሚካሄድ በዝርዝር የተገለጸ ነገር የሌለ ሲሆን፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች መንግስት አካሄደዋለሁ የሚለው ምርመራ ተዓማኒነት እንደማያገኝ ይነገራል።

በሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በመባባስ ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት ድርጊቱን ለመቆጣጠር በሚል የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።

ይሁንና አሜሪካና በርካታ አለም አቀፍ ተቋማት አዋጁ ስጋት እንዳሳደረባቸው በመግለፅ ከመንግስት ማብራሪያ እየጠየቁ ይገኛል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የአስቸኳይ አዋጁ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ያባብሳል ሲሉ ቅሬታን አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ ባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዙሪያ ለሁለተኛ ጊዜ ስጋቷን የገለጸችው አሜሪካ አዋጁ ከህዝብ እየቀረቡ ላሉ ጥያቄዎች መፍትሄን ለማፈላለግ ያለመ መሆን እንዳለበት አሳስባለች።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ጆን ከርቢ አዋጁ እየቀረቡ ያሉ ድምጾችን ለማፈን መዋል የለበትም ሲሉ መግለጻቸውን አዣንስ ፍራስ ፕሬስ ዘግቧል።