የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህዝባዊ ተቃውሞ እያባባሰው ሊሄድ እንደሚችል ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ዘገበ

ኢሳት (ጥቅምት 3 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሃገሪቱ በመስፋፋት ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ከመቆጣጠር ይልቅ እያባባሰው ሊሄድ እንደሚችል ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ አቋሙን በሚገልጽበት ርዕሰ አንቀጹ ባልስተላለፈው መልዕክት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አመራሮች ስኬት ሊያመጣ ያልቻለውን የአፈና ፖሊሲያቸውን አጠናከረው ቀጥለዋል ሲል የገለጸው አለም አቀፍ ጋዜጣው፣ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዚህ ማሳያ መሆኑን በጽሁፉ አትቷል።

ተግባራዊ ተደርጎ በሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችን ለመከልከል ያለመ ቢሆንም ይኸው መብት ቀድሞውኑ የተገደበ እንደነበር ከአንድ ወር በፊት ተመሳሳይ አቋሙን በርዕሰ አንቀጹ አስተላልፎ የነበረው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ አመልክቷል።

የመንግስት ባለስልጣናት በሃገር ውስጥ እየተባባሰ ላለው ተቃውሞ የውጭ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ቢሞክሩም ድርጊቱ ዕውነታን የመሸፋፈን ነው ሲል ጋዜጣው አስነብቧል።

በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ከህዝብ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽን ከመስጠት ይልቅ ጥይትን እንደመፍትሄና ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መቀጠሉን በርዕሰ-አንቀጹ ተገልጿል።

አሜሪካና ምዕራባውያን ከሃገሪቱ ጋር በሽብርተኛ ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ቅድሚያ በመስጠት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ችላ ማለት እንደማይገባቸውና ዕርምጃን መውሰድ እንዳለባቸው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ በጽሁፉ አስፍሯል።

ለስድስት ወር ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አምባገነን መንግስታት ተቃውሞን ለማፈን የሚጠቀሙበት ስልት እንደሆነ ያወሳው ጋዜጣው ዕርምጃው የሚያመጣው ነገር እንደሌለ አክሎ ገልጿል።

በአለም ዙሪያ ተነባቢ የሆነው ጋዜጣው በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ አሜሪካና ምዕራባውያን ግልጽ የሆነ አቋም እንዲከተሉና በተግባር እንደሚያሳዩ ሲጠየቅ መቆየቱ ይታወሳል።