በኦሮሚያ ክልል ከተሞች አባላትን ለመመልመልና ስልጠና ለመስጠት ሞክረዋል የተባሉ የሽብረተኛ ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው

ኢሳት (ጥቅምት 2 ፥ 2009)

በአሜሪካ ይገኛል ከተባለው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የስልክ ግንኙነት በማድረግ በአዲስ አበባና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች አባላትን ለመመልመልና ስልጠና ለመስጠት ሞክረዋል የተባሉ 17 ተጠርጣሪዎች የሽብረተኛ ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።

ገንዘብ ተቀብለዋል የተባሉት እነዚሁ ተጠርጣሪዎች ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ሰበታ፣ ጅግጅጋ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች እንደሆነ ረቡዕ ክሳቸው መነበብ መጀመሩን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ጫካዎችን በማጥናት፣ ወታደራዊ ካምፕ በመመስረት እና አባላትን በድብቅ በማደራጀት ወታደራዊ ስልጠና ሰጥተዋል ሲል በጠቅላይ አቃቢ ህግ በክሱ አስፍሯል።

ይሁንና አቃቤ ህግ በተጠርጣሪዎች ምን ያህል ሰዎች እንደተመለመሉና ስልጠና እንደወሰዱ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ ከአንድ ግለሰብ ጋር በስልክ ግንኙነት በማድረግ 157ሺ ብር መቀበላቸው ተመልክቷል።

የሽብርተኛ ክስ የተመሰረተባቸው እነዚሁ ተጠርጣሪዎች በቀረበባቸው ክስ ላይ ተቃውሟቸውን እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ለጥቅምት 22, 2009 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮን ሰጥቷል።

መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተግባራዊ ካደረገ በኋላ ክሱ ሲመሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።