አሜሪካ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠየቀች

ኢሳት (ጥቅምት 2 ፥ 2009)

አሜሪካ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገዥው የኢህአዴግ መንግስት “ራሱን ለመከላከል የወሰደው ስልት ነው” በማለት ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠየቁ።

የሰዎች መሰባሰብን፣ ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽና ያለፍርድ ቤት ሰዎችን ለማሰር ስልጣን ያለው አዋጁ በምን ሁኔታ ተግባራዊ ሊደረገ እንደታሰበ የኢትዮጵያ መንግስት ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት ይኖርበታል ሲል የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ለአለም አቀፍ መገንኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሃገራት ኤምባሲዎችና አለም አቀፍ ተቋማት የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ በይፋ ቅሬታውን ያቀረበው የአሜሪካ መንግስት እየተሰሙ ያሉ ድምጾችን ለመቆጣጠር የተወሰደው እርምጃ ችግሩን ሊያባብሰው እኝደሚችል መግለጹን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ረቡዕ ዘግቧል።

መቀመጫቸውን በዚህ በአሜሪካ ላደረጉ አለም አቀፍ መገናኛ ተቋማት መግለጫን የሰጡት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ መንግስት የወሰደው ዕርምጃ ራስን ለመከላከል የተወሰደ ስልት እንደሆነም አስታውቀዋል።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለስድስት ወራቶች ተግባራዊ ተደረጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ሊያባብስ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ጉብኝቱን እያደረጉ ያሉት የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርከል መንግስት በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚወስደውን ዕርምጃ በማቆም ጥያቄን እያቀረቡ ላሉ አካላት ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

የአዋጁ መውጣት ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች እንዲሰማሩ ተደርጎ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችን እንዲቆጣጠሩና ሰዎችን እንዲያስሩ የፈለጉት ምርመራ እንዲያካሄዱ መብትን ይሰጣል።

ይሁንና ገዢው የኢህዴግ መንግስት የወሰደው ዕርምጃ ተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲባባስ የሚያደርግ እንደሆነ የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

መቅረብ የጀመረውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተቀመጠው ጊዜ በታች ሊጠናቀቅ ይችላል ሲል ማክሰኞ ማስታወቁ ይታወሳል።