ጥቅምት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በባህር ዳር ከተማ በተደጋጋሚ በተጠሩት የስራ ማቆም አድማዎች አንድነቱን ያሳየው የባህር ዳር ከተማ ማህበረሰብ ለስርዓቱ አንገዛም የሚለውን መፈክር አሁንም በማሳየት የስራ ማቆሙን አድማ ለሁለተኛ ቀን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በትላንትናው እለት በተካሄደው የስራ ማቆም አድማ እንዳይሳተፉ ጫና ተደርጎባቸው ከሰዓት በኋላ የተከፈቱ የአዴት ተራ ሱቆች ዛሬ በእምቢተኝነታቸው በመጽናት ከሌላው ማህበረሰብ ጋር የአድማው ተሳታፊ በመሆን ሱቆቻቸውን ዘግተዋል፡፡ በከተማዋ ከተወሰኑ ታክሲዎች በስተቀር ሁሉም የህንጻ መሳሪያና ሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች፣የሞባይል መሸጫ መደብሮች ሆቴል ቤቶች፣ ካፌዎችና ሶስቱም ገበያዎች በስራ ማቆም አድማው ተካፋይ ናቸው፡፡ለስርዓቱ ያላቸውን ተቃውሞ በስራ ማቆም አድማው በመግለጽ ላይ ያሉት የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ፣ አድማውን ለ5 ቀናት ያካሂዷል።
በከተማዋ የሚገኙ ወፍጮ ቤቶችና አነስተኛ የኮንቴንር ሱቆች ለህብረተሰቡአገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተዘዋውረው የተመለከቱት ሪፖርተሮች አረጋግጠዋል፡፡
በሌላ በኩል በሰፈነ ሰላም ክፍለ ከተማ ውስጥ ድብ አንበሳ ሆቴል ጀርባ ጆን ባር ምሽት ቤት አካባቢ በስርዓቱ ወታደሮች ላይ በተወረወረው የእጅ ቦምብ አራት ያህል ወታደሮች መቁሰላቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ በመኪና ላይ ሆነው ቅኝት ሲያደርጉ በነበሩ ሁለት መኪኖች ላይ በተሳፈሩ የስርዓቱ ወታደሮች ላይ የተወረወረው ይህ የእጅ ቦምብ መኪኖችን ስቶ በአቅራቢያቸው ላይ በመውደቁ ዳር ላይ የተቀመጡ ሶስት የስርዓቱ ወታደሮች ቀላል ቁስለኛ ሲሆኑ አንድ ወታደር ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶበታል፡፡
የእጅ ቦምቡ በተጣለበት አካባቢ በጫት ቤት ሽያጭ ላይ የነበረን አንድ ወጣት ወታደሮች ‹‹የወረወሩትን ተናገር !!›› በማለት ከታቀፈው ህጻን ልጁ በመለየት ከፍተኛ ድብደባ በማድረስ የአካል ጉዳት ያደረሱበት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በዛሬው እለት ተመሳሳይ ጥቃት ይፈጸማል በሚል ፍራቻ ከተማዋ በከተማ ፖሊስና በክልሉ አድማ በታኝ ፖሊሶች ተወራለች፡፡በሁሉም አካባቢ የታጠቁ ወታደሮችና የፖሊስ ሰራዊት አባላት በብዛት ይታያሉ፡፡
ከባህርዳር ወጣ ብሎ በሚገኘው አንዳሳ ቀበሌ ደግሞ ተማሪዎች አርማ ያለበት ሰንደቃላማ ወርዶ አርማ በሌለበት ሰንደቃላማ ካልተተካ አንማርም በማለት ዛሬ መጠነኛ ተቃውሞ አሰምተዋል።
በሌላ በኩል ነገ ሃሙስ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴን ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በርካታ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከባህርዳር ተነስተው ወደ ጎንደር አምርተዋል። ኮሎኔል ደመቀ ከጎንደር ይወጣሉ የሚል ፍርሃት መኖሩን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።