ህዳር 13 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በእነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱት 24 የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላት፣ ጋዜጠኞች እና ነፃ አሳቢ ዜጎች የክስ ቻርጅ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ጠዋት ቀርቦ ተነበበ፡፡
ከጠዋቱ 3፡40 ሰዓት ላይ በካቴና ታስረው ወደ ችሎት የቀረቡት በሀገር ውስጥ የሚገኙት ከተራ ቁጥር 1 እስከ ተራ ቁጥር 8 ያሉት ተከሳሾች ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ከሀገር ውጪ በመሆናቸው በጋዜጣ ተጠርተው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም አዞ ነበር፡፡
በችሎቱ ላይ የቀረቡት ተከሳሾች በሙሉ የመጎሳቆል፣ በአካላቸውም የመክሳት ሁኔታ ቢታይባቸውም፣ የክስ ቻርጁ ሲነበብ የፌዝ ፈገግታ በማሳየት በክሱ ላይ ተቃውሟቸውንና በፍርድ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንደሌላቸው አመላክተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የግል ማህበራዊ መረጃቸውን ሲጠይቅ፣ አንደኛ ተከሳሽ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንዷለም አራጌ የሥራውን ሁኔታ ሲጠየቅ የሙሉ
ሰዓት ፖለቲከኛ ብሎ የተናገረ ሲሆን፣ 5ተኛ ተከሳሽ ክንፈሚካኤል ደበበ በረደድ (አበበ ቀሲቶ) ለሰው ልጆች ፍትህና ሠላም መስፈን የምንቀሳቀስ ሠላማዊ ታጋይ ነኝ በማለት ራሱን አስተዋውቋል።
8ተኛ ተከሳሽ አንዷለም አያሌው ገላው ለጊዜው ሥራ የለኝም፣ ከምኖርበት ካርቱም የስደተኛ ጣቢያ ነው ተይዤ የመጣሁት፤ ስለዚህ አድራሻ የለኝም፣ ቀደም ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላ ሳለሁ የተሰጠኝን ቤት ባለቤቴንና ሁለት ልጆቼን አስወጥተው በአሁኑ ሰዓት የት እንዳሉ እንኳ አላውቅም ብሏል፡፡
አቃቤ ሕግ ባቀረበው የክስ ቻርጅ ላይ ማረሚያ አለኝ በማለቱ ፍርድ ቤቱም አጽድቆለት በሁሉም ተከሳሾች ላይ አቅርቦት የነበረውን 1ኛ ክሥ፣ ከ1ኛ ተከሳሽ እስከ 22ተኛ ተራ ቁጥር ተከሳሽ ብቻ ይሁንልኝ በማለት የቀድሞው አዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና ማኔጂንግ ኤዲተር መስፍን ነጋሽና ዐብይ ተክለማርያም ላይ ከአንደኛው ክስ ውጪ አድርጓቸዋል፡፡
ዐቃቤ ህግ ባቀረበው የክስ ቻርጅ ላይ በሁለተኛው ክሥ ከተከሳሽ ተራ ቁጥር 1 እስከ 18 ድረስ የሚለውን በ21ኛ እና በ22ተኛ ተራ ቁጥር ተከሳሾችም ላይ እንዲካተት ያደረገ ሲሆን፣ በ2ተኛው ክሥ 2ተኛ መስመር ላይ ከ2 እስከ 6ተኛ ተራ ቁጥር የሚለው ላይ 7ተኛ ተራ ቁጥርም በክሱ ላይ እንዲካተት አድርጓል፡፡
የተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው በክሱ አቀራረብ ላይ ተቃውሟቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ በተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ፣ በሽ ብርተኝነት፣ በሀገር መክዳትና የስለላ ተግባር ሲሆን፣ ይህም ከእድሜ ልክ እስከ ሞት
ፍርድ ድረስ የሚያስቀጣ ቢሆንም ዐቃቤ ህግ ባቀረባቸው የክስ ቻርጅ ላይ ይህን የሚያመለክት የህግ መርሆዎችን የማያሟላ ተራ አሉባለልታ እና ተከሳሾቹ በህገ መንግሥቱ መሠረት በህግ ተቋቁሞ በሰላማዊ መንገድ የሚታገል የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አባላት እና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በመጠቀም የሚሰራ የጋዜጠኝነትና የፖለቲካ ትንታኔ ሥራዎች የሚያከናውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በህጋዊ ሥራዎቻቸውና በግል መብታቸው ነው የተከሰሱት በማለት አብራርተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ በቅርቡ ከወሰነው የግንቦት 7 አመራር አባላት ጋር አንድ ላይ መከሰሳቸው ዐቃቤ ህግ ሆን ብሎ በተከሳሾቹ ላይ ጉዳት ለማድረስና ጫና ለመፍጠር ነው ሲሉ ጠበቆች አክለዋል፡፡
ዐቃቤ ህግ ባቀረበው የክሥ ቻርጅ ላይ ከአሸባሪ ጋር በመገናኘት፣ ድጋፍ በመስጠት፣ ሀገር በመክዳት፣ በመሰለል የሚሉ ቃሎች አሉ ያሉት የተከላካይ ጠበቆች ነገር ግን ወንጀሉ የተፈጸመበትን ጊዜና ቦታ አላስቀመጠም በማለት ሰፊ ህጋዊ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግን ክስና የተከላካይ ጠበቆችን መቃወሚያ ካደመጠ በኋላ በክሥ ቻርጁ ላይ ብይን ለመስጠት ለነገ ሃሙስ ህዳር 14 ቀን 2004 ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ተበትኗል፡፡