በምዕራብ አርሲ ዞን ባልና ሚስትን ጨምሮ በትንሹ ሶስት ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች ተገደሉ

ኢሳት (ጥቅምት 1 ፥ 2008)

በምዕራብ አርሲ ዞን ስር በምትገኘው የቡልቻና ከተማ በመካሄደ ላይ ያለን ተቃውሞ ለመቆጣጠር የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ ባልና ሚስትን ጨምሮ በትንሹ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን ዕማኞች ለኢሳት አስታወቁ።

በቅርቡ በቢሾፍቱ ከተማ የደረሰውን ዕልቂት ተከትሎ በምስራቅና ምዕራብ አርሲ ዞኖች ስር በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞ በአዲስ መልክ መቀስቀሱ ይታወቃል።

ይኸው ተቃውሞ በቡልቻና ከተማ ከቀናት በፊት መካሄድ መጀመሩን ለዜና ክፍላችን የተናገሩት ነዋሪዎች በአካባቢው ሰፍረው የሚገኙ የአጋዚ ወታደሮች ባልና ሚስት ላይ አሰቃቂ ነው ያሉት ግድያ መፈጸሙን አስረድተዋል።

ይኸው ተቃውሞ በቡልቻና ከተማ ከቀናት በፊት መካሄድ መጀመሩን ለዜና ክፍላችን የተናገሩት ነዋሪዎች በአካባቢው ሰፍረው የሚገኙ የአጋዜ ወታደሮች ባልና ሚስት ላይ አሰቃቂ ነው ያሉት ግድያ መፈጸሙን አስረድተዋል።

የባልና ሚስቱ የቀብር ስነ-ስርዓት ሰኞ በተፈጸመበት ወቅት ሃዘንተኞች ተጨማሪ ተቃውሞ ማሰማት በጀመሩ ጊዜ የጸጥታ ሃይሎች ዳግም ዕርምጃ በመውሰድ አንድ ወጣት መግደላቸውም ታውቋል።

የዚሁ ወጣት የቀብር ሰነስርዓት ማክሰኞች የተከናወነ ሲሆን፣ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች እየወሰዱት ያለው የሃይል ዕርምጃ ለደህንነታቸው ስጋት መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማ ከአንድ ሳምንት በፊት የደረሰውን ዕልቂት ተከትሎ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ዳግም የተቀሰቀሱ ሲሆን፣ መንግስት ይህንኑ ተቃውሞ ዕልባት ለመስጠት በሚል ከቅዳሜ ጀምሮ ተግባራዊ የሆነ የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።

ይሁንና ተቃውሞው አሁንም ድረስ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል በመካሄድ ላይ መሆናቸው ከሃገር ቤት ከሚደርሱን መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።