ኢሳት (መስከረም 30 ፥ 2008)
መንግስት ለስድስት ወር የሚቆይ የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አለም አቀፍ ተቋማትና የሃገር ውስጥ ተወካዮች በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ጠየቁ።
ከቅዳሜ ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ይኸው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አለም አቀፍ ህጎችና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን የሚጥስ አይደለም ቢባልም የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ለኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረባቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል።
ሶስተኛ ቀኑን የያዘው አዋጅ በአለም አቀፍ ተቋማት የስራ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩን እነዚሁ አካላት በዋነኛነት ማንሳታቸው ታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን በቀጣዮቹ ቀናቶችን ለመስጠት በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ለኢሳት ገልጸዋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአዋጁ ደንብ የሰዓት ድንጋጌን ቢፈቅድም ለጊዜው በሃገሪቱ የሰዓት ዕላፊ ገደብ አለመቀመጡን በመግለጫው አመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ በአዲስ መልክ ተባብሶ መቀጠሉን መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ ዋጅ እንዲወስድ ማስገደዱን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይገልጻል።
በአሁኑ ወቅት ተቃውሞን ለመቆጣጠር ተሰማርተው የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች ድርጊቱን ለመቆጣጠር እንደተሳናቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ መንገስት በአዲስ መልክ ሊወስድ ስላሰልበው እርምጃ ግን የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
ይሁንና መንግስት ተግባራዊ ያደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ተጨማሪ የሃገሪቱ የመከካለከያ ሰራዊት ተቃውሞችን ለመቆጣጠር እንደሚሰማራ ቢቢሲ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት ዘግቧል።
በዚሁ አዋጅ መሰረት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች እንዳይካሄድ የተካተተ ሲሆን ተቃውሞዎች ቢካሄዱ የመከላከያ ሰራዊት ዕርምጃ እንዲወስድ ልዩ ትዕዛዝ እንደተሰጠው ለመረዳት ተችሏል።
የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች እንዳይካሄዱ የተላለፈው ውሳኔ የሃገሪቱን የጸጥታና የህዝባችንን ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል ነው ስሉ የመንግስት ቃለ-አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ ተናገረዋል።
በህዝቡ ተወካዮች ምክር ቤት ያልጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰኞ ስራውን በጀመረው ፓርላማ ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል። ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው ይኸው አዋጅ ሲወጣ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ታውቋል።