የአውሮፓ ህብረት የማሻሻያ እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ ጠየቀ

ኢሳት (መስከረም 30 ፥ 2008)

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በሃገሪቱ የማሻሻያ ዕርምጃዎችን ተግባራዊ እንዲደረጉ ሰኞ ጠየቀ።

በወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በተያዘው ወር ሁለተኛ መግለጫውን ያወጣው ህብረቱ ሁሉንም ወገኖች የሚያሳትፍ የማሻሻያ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰቡን ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይምስ ጋዜጣ ህብረቱን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ስላለው አለመረጋጋት ስጋቱን ገልጾ የነበረውን የኢትዮጵያ የልማት አጋር የሆነው የአውሮፓ ህብረት በሃገሪቱ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ አሳስቦት እንደሚገኝ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ህዝባዊ ተቃውሞ ዘገባን ያቀረበው ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይምስ ጋዜጣ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞን ለመቆጣጠር በወሰዱት የሃይል ዕርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን አውስቷል።

ከማከስኞ ጀምሮ በኢትዮጵያ ጉብኝትን የሚያደርጉትን የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርከል በሃገሪቱ በሚኖራቸው ቆይታ በወቅታዊው የኢትዩኦጵያ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ በኢትዮጵያ ጉብኝትን ለማድረግ የመጀመሪያ የሆኑት መርከል በመንግስት በኩል በፓርላማ ንግግርን እንዲያደርጉ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ “ከአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ስር በዋለ ፓርላማ ውስጥ ንግግርን ማድረግ ምንም ለውጥ አያመጣም” በማለት ግብዣውን እንዳልተቀበሉት ሪፖርተር ዘግቧል።

ይሁንና የጀርመኗ ቻንስለር ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በሚያደርጉት ውይይት በተጨማሪ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር በጀርመን ኢምባሲ እንደሚመክሩ ታውቋል።

በማሊና ኒጀር ተመሳሳይ ጉብኝትን የሚያደርጉት መርከል መንግስታቸው በአፍሪካ ህብረት የሰላምና የጸጥታ ምክር ቤት ያስገነባውን ህንጻ ይመርቃሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣንት ጋርም በአህጉሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ መረዳት ተችሏል።