የግብጽ መንግስት በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ አልገባሁም አለ

ኢሳት (መስከረም 30 ፥ 2008)

የግብጽ መንግስት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጣልቃ አለመግባቱን ሰኞ ለኢትዮጵያ በሰጠው ምላሽ አስተባበለ።

የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባ አህመድ አቡ ዘይድ ሃገራቸው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳልገባች በመግለጽ በሁለቱም ሃገራት መካከል በከፍተኛ አመራሮች ምክክር በመካሄድ ላይ መሆኑን ለአዣንስ ፍራስ ፕሬስ አስታውቀዋል።

የኢትጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ግብጽ በመካሄድ ላይ ካለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጀርባ እጇ እንዳለበት ይፋዊ መግልጫ መስጠቱ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አዲስ አበባ የሚገኙትን የግብፅ አምባሳደር በመጥራት በጉዳዩ ዙሪያ መምከሩም የሚታወቅ ነው።

በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ምላሽን የሰጠው የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን አስተባብሏል።

በ24 ሰዓታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መግለጫን የሰጠው የሃገሪቱ መንግስት የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት በከፍተኛ ባለስልጣናት በኩል ምክክር እየተደረገ መሆኑን አክሎ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከግብጽ በኩል ድጋፍ ይደረግለታል ሲሉ በድጋሚ መናገራቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።

በአባይ ግድብ ጉዳይ ባለመግባባት ውስጥ የቆዩት ሁለቱ ሃገራት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ እንዲህ ያለ ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ታውቋል።